
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በ2017 ዓ.ም የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አባላትን ለማሳደግ በዞን እና በወረዳዎች የንቅናቄ መድረክ ሲካሄድ መቆየቱን የአማራ ጤና ቢሮ የሃብት አሠባሠብ አሥተዳደር እና አጋርነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አዲሱ አበባው ተናግረዋል፡፡
በ2016 ዓ.ም በተፈጠረው ሀገራዊ የሰላም እጦት ምክንያት የተጠቃሚዎች ቁጥር በእጅጉ መቀነሱን የገለጹት ዳይሬክተሩ ከጥር 01/2017 ዓ.ም ጀምሮ አባል የማፍራት ሥራ እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡
አባል የማፍራት ሥራ ሲባል ባለፈው ዓመት የነበሩትን በማደስ የማስቀጠል እና አዲስ አባላትን ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ እንደኾነም ነው የተናገሩት፡፡ይህ ሥራ በጥር ወር
ብቻ የሚከወን ሥራ እንደኾነም ጠቁመዋል፤ የጥር ወር ካለፈ ግን ማንኛውም ሰው አባል መኾን አይችልም ነው ያሉት፡፡
ከዚህ በፊት በክልሉ 10 በመቶ ሕዝብ ብቻ የጤና መድኅን አገልግሎት ሲያገኝ ስለመቆየቱም ነው ያስረዱት፡፡ ከዚህ ዓመት ጀምሮ ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ሁሉንም ማኅበረሰብ ወደ ጤና መድኅን አገልግሎት ለማስገባት የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁንም ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡
በዚህም በ1 ቢሊዮን ብር 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ለሚኾኑ መክፈል ለማይችሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች የክልሉ መንግሥት እና 25 በመቶ በፌዴራል መንግሥት ድጎማ ወጫቸው ተሸፍኖ የጤና መድኅን አባል እንዲኾኑ የማድረግ ሥራ እየተሠራ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክተሩ የጤና መድኅን አባል ለመኾን መመዝገብ የሚቻለው በጥር ወር ብቻ መኾኑን ሁሉም ተረድቶ አባል እንዲኾን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከጥር 1/2017 ዓ.ም እስከ ጥር 30/2017 ዓ.ም ባሉ ቀናቶች በመመዝገብ ደብተሩን እንዲይዝ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!