
ደባርቅ: ታኅሣሥ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎንደር ዞን የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት የመክፈል ዓቅምን መሠረት ያደረገ የማኅበረሰብ ዓቀፍ ጤና መድኅን ዓመታዊ መዋጮ አፈጻጸም የሥልጠና እና የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።
በሥልጠና እና የንቅናቄ መድረኩ የቀበሌ አሥተዳዳሪዎች፣ የጤና ኤክስቴንሽ ባለሙያዎች እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። ወይዘሮ የሽ ሽፈራው የደባርቅ ከተማ ነዋሪ እና የጤና መድኅን ተጠቃሚ ናቸው። በመድኃኒት ግዥ ወቅት ከውጭ እንድንገዛ እንደረጋለን ሲሉ ተናግረዋል። በአንዳንድ የጤና ባለሙያዎች ላይም የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ቅሬታ እንዳላቸውም ገልጸዋል።
የክራር ቀበሌ ዋና አሥተዳዳሪ ፈንታው ጎሼ የጤና መድኅኑ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል። ከጊዜ ወደ ጊዜ የጤና መድኅን ተጠቃሚው ቁጥር እያደገ መምጣቱን የገለጹት የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ያብባል ሀብቴ ናቸው።
ባሳለፍነው የ2016 በጀት ዓመት ብቻ በከተማዋ ከ35 ሺህ በላይ ነዋሪዎች የጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ መኾናቸውን ገልጸዋል። ኀላፊው የወጭ እና ገቢ አለመመጣጠን ችግር እንደገጠማቸው ገልጸው የመክፈል ዓቅምን መሠረት ያደረገ መዋጮ ማስተካከል መቻሉን አንስተዋል።
የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት የጤና መድኅን ቡድን መሪ አበበች ብርሃኔ በከተማዋ ካሉ ተጠቃሚዎች መካከል ከ42 በመቶ በላይ የሚኾኑት ተመላላሽ ታካሚ መኾናቸውን ተናግረዋል።የጤና መድኅን አገልግሎት ለታካሚዎቹ ያለው ፋይዳ የጎላ ነውም ብለዋል።
“የጤና መድኅን ወጭው ከፍተኛ ቢሆንም የሰውን ሕይዎት መታደግ እስከቻለ ድረስ እንደ ኪሳራ አናየውም” ነው ያሉት። በቀጣይም የተነሱ ሐሳቦችን እንደ ግብዓት በመጠቀም የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ከሚመለከታቸው አጋር ተቋማት ጋር እንደሚሠራ ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!