
ወልድያ: ታኅሣሥ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) መቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማኅበር በሰሜን ወሎ ዞን በቡግና ወረዳ የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ድጋፍ አድርጓል።
ድጋፉን ያስረከቡት የመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማኅበር የሕክምና ቡድን አሥተባባሪ ዮናስ ሙሉጌታ የመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማኅበር ባለፉት ዓመታት በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።
መቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማኅበር በሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ በተፈጠረው ችግር ምክንያት የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጋቸውን ነው የገለጹት። ድጋፉ የሕጻናት አልሚ ምግቦችን ጨምሮ ሌሎችን ያካተተ መኾኑን ነው የተናገሩት። የተደረገው ድጋፍ 15 ሚሊዮን ብር እንደሚገመትም አመላክተዋል። ድጋፉን ራሳቸው ለተጎዱ ወገኖች እንደሚያደርሱም ገልጸዋል።
መቄዶንያ በጎ አድራጎት ማኅበር ሰው ለመርዳት ሰው መኾን በቂ ነው በሚል መርሕ ካለው ላይ ድጋፍ ማድረጉን ነው የተናገሩት። ኢትዮጵያን በራሳችን አቅም ለራሳችን ወገን መድረስ እንችላለንም ብለዋል። በቡግና ወረዳ የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል። ድጋፎቹን በቀጣይ ወራትም አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ነው ያመላከቱት።
ሁሉም በመረባረብ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ማድረግ አለበት ብለዋል። የበጎ አድራጎት ማኅበሩ ድጋፍ ያደረገው ከተሰጠው ላይ መኾኑን ገልጸዋል። የመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማኅበር ላሊበላ ቅርንጫፍ የችግሩን አሳሳቢነት ቦታው ድረስ በመሄድ ማየቱንም አንስተዋል። ሰብዓዊ ድጋፍ ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች በቡግና ወረዳ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የቡግና ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ገብረመስቀል ዓለሙ በቡግና ወረዳ በተከሰተው የምግብ እጥረት ምክንያት እናቶች እና ሕጻናት ለሥርዓተ ምግብ ችግር ተጋላጭ መኾናቸውን ገልጸዋል።
አሁን ላይ በወረዳው በችግር ውስጥ ላሉ ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ እየተሠራ ያለው ሥራ መልካም መኾኑንም ተናግረዋል። በመንግሥት፣ በበጎ አድራጎት ማኅበራት እና ድርጅቶች፣ በግለሰቦች አልሚ ምግቦች እና ሌሎች ድጋፎች እየቀረቡ መኾናቸውን ነው የገለጹት።
የመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማኅበር ያደረገውን ድጋፍ ለተጎጂ ወገኖች እንደሚደርስም ተናግረዋል። መቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማኅበር ላደረገው ድጋፍም ምሥጋና አቅርበዋል።
እስካሁን ድረስ ድጋፍ ላደረጉ ሁሉ ምሥጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት። ከችግሩ ሥፋት አንጻር የሚደረገው ድጋፍ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!