“እንግዶቻችንን በሰላም ሸኝተናል” የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር

42

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም በደማቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ተከብሯል። በበዓሉ በርካታ እንግዶች ተገኝተዋል። የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ባቀደው ልክ በዓሉን አክብሮ ማጠናቀቁን አስታውቋል።

የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ወንድምነው ወዳጅ የልደት በዓል በላሊበላ በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ አቅደው ሢሠሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል። እንግዶች በሰላም ገብተው በሰላም እንዲወጡ እና በዓሉን በሰላም እንዲያከብሩ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ እንደነበር ነው የተናገሩት።

በዓሉ ከመጀመሪያው ከቅድመ ዝግጅት እስከ ማጠቃለያው ድረስ ፍጹም ሰላም ኾኖ ተጠናቅቋል ነው ያሉት። እንግዶች በእግር እና በተለያዩ የትራንስፖርት አማራጮች በስፋት መግባታቸውንም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባመቻቸው የበረራ አማራጭ እና ተጨማሪ በረራ በርካታ እንግዶች ወደ ከተማዋ መግባታቸውን ነው ያስታወሱት። እንግዶችን በሰላም ተቀብለን፣ በዓሉን በሰላም እንዲያከብሩ በማድረግ፣ በሰላም ተመልሰዋል ነው ያሉት።

በዓሉ ሃይማኖታዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በድምቀት መከበሩን እና ሰላም የተሰበክ መኾኑንም ገልጸዋል። በፍጹም ሰላም ተጀምሮ በፍጹም ሰላም ተጠናቅቋል ነው ያሉት።
የልደት በዓል በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ ላደረጉ፣ እንግዶችን በፍቅር እና በትህትና ለተቀበሉ፣ ለበዓሉ ድምቀት የራሳቸውን አስተዋጽኦ ላደረጉ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ የጸጥታ አካላት ምሥጋና አቅርበዋል። ሚዲያዎች ለበዓሉ ድምቀት ላደረጉት አስተዋጽኦ አመሠግነዋል።

በዓሉ ላሊበላ ዕውነተኛ የኢትዮጵያ የታሪክ ባለቤት መኾኗን ያሳየችበት፣ ዳግማዊት ኢየሩሳሌምነቷን ያስመሰከረችበት ነው ብለዋል። የከተማዋ ሕዝብ በዓሉን በዓመት አንድ ጊዜ የሚያገኘው እና በጉጉት የሚጠብቀው በመኾኑ እንዲስተጓጎልበት አይፈልግም ነው ያሉት። የከተማ ነዋሪዎች ለሰላም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ስላደረጉ በዓሉ በሰላም ተጠናቅቆ እንግዶች በሰላም እንዲሸኙ ኾኗል ብለዋል።

የጠበቅነውን አሳክተናል ነው ያሉት። በበዓሉ የከተማዋ ነዋሪዎች መልካም እሴት እንደተገለጠም ገልጸዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች እግር አጥበው ተቀብለው፣ ጾም አስፈትተው መሸኘታቸውንም ተናግረዋል።

በዓሉ ለቀጣይ የቱሪዝም እንቅስቃሴ መሠረት እንደሚጥል ተናግረዋል። በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎች በበዓሉ ላይ መታደማቸውንም ገልጸዋል። በዓሉን የቅዱሱ እና የንጉሡ ልጆች መኾናችን አሳይተንበታል ነው ያሉት። ላሊበላ የኢትዮጵያ ኩራት መኾኗን አሳይታለች ብለዋል።

የላሊበላ ከተማ ድንቅ እና ብርቅ ሃብት እንዳላት የተናገሩት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው እንግዶች በስፋት ላሊበላን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል። የቱሪዝም እንቅስቃሴውን የበለጠ ለማጠናከር ሰላም ላይ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል። ሰላም ካለ ቱሪዝም አለ፣ ቱሪዝም ካለ ሰላም አለ ነው ያሉት። እጥፍ ድርብ ተስፋ ያየንበትን የልደት በዓል አሳልፈናልም ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የተሰበሰበው ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የ8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ብልጫ አለው” የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ
Next articleመቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማኅበር በቡግና ወረዳ ድጋፍ ለሚፈልጉ ወገኖች ድጋፍ አደረገ።