
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 30/2017 ዓ.ም(አሚኮ) የተሰበሰበው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር ሲታይ ከ8 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ ማሳየቱን የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል።
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ በ2017 በጀት ዓመት ከመደበኛ እና ከከተማ አገልግሎት 71 ነጥብ 56 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ዓቅዶ እየሠራ ይገኛል። እስከ ታኅሣሥ 23/2017 ዓ.ም ድረስ 25 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን በቢሮው የግብር ትምሕርት እና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ታዘባቸው ጣሴ ለአሚኮ ገልጸዋል።
የገቢ አሰባሰቡ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ8 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ አሳይቷል ብለዋል። ሰሜን ሽዋ፣ ደቡብ ወሎ ፣ ዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር፣ ኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር፣ ደሴ ከተማ አሥተዳደር እና ሰሜን ወሎ ዞን የተሻለ ገቢ ከሰበሰቡት ውስጥ ይጠቀሳሉ ነው ያሉት።
የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱን ለማዘመን የኤሌክትሮኒክስ ታክስ አሥተዳር ሥርዓት በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በሁሉም ክፍለ ከተሞች መጀመሩን ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።
አሠራሩን ወደ ሌሎች ከተሞች እና ዞኖች ለማስፋት ቅድመ ዝግጅት ተደርጓልም ብለዋል።
በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር መሻሻል ቢያሳይም አሁንም ግን በአንዳንድ አካባቢዎች በአካል ድጋፍ ለማድረግ ችግር መኾኑን ገልጸዋል። አንዳንድ ግብር ከፋዮች በክልሉ የተፈጠረውን የሰላም እጦት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ደረሰኝ የማይቆርጡ እንዳሉም አንስተዋል።
“የክልሉን ዕድገት ለማፋጠን እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት ግብር መዘንጋት የሌለበት” በመኾኑ ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
ማኅበረሰቡም የታቀደው ግብር እንዲሳካ በግብር አሠባሰብ ሂደቱ አጋዥ እንዲሆን አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!