
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አምላክ ተወልዷልና የጨለማው ዘመን አልፏል። ድቅድቁ ጨለማ በእርሱ ብርሃን ተገፍፏል። የተመረጠችው ቤተልሔም ጌታ ተወልዶባታል። ከዳር እስከ ዳር፣ ከመሬት እስከ ሰማይ በብርሃን ተመልቷል። መላእክት በሰማያት ያመሰግናሉ። በአርያም ስብሐት ይላሉ። እረኞች በከብቶች በረት ለጌታቸው ይዘምራሉ። ፍጥረታት የፈጣሪያቸውን ድንቅ ሥራ እያዩ ይደነቃሉ። ሰማያት በምስጋና ተሞልተዋል። መላእክት በጌታቸው ትህትና ተደንቀዋል።
ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም በተወለደ ጊዜ መላእክት በሰማያት እንደዘመሩለት፣ እረኞች በምድር እንዳዜሙለት፣ ምስጋናም እንዳቀረቡለት ሁሉ በደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላም ሊቃውንት በመላእክት እና በእረኞች ተመስለው ጌታቸውን ያመሰግኑታል። ውዳሴም ያቀርቡለታል።
በላሊበላ አብያተክርስቲያናት በቤተ ማርያም፣ የአርያም እና የምድር ምሳሌ በኾነው ሥፍራ ልብሰ ተክህኗቸውን ለብሰው ቤዛ ኩሉ እያሉ ይዘምራሉ። ለጌታቸውም በትህትና ይሰግዳሉ። ቤተልሔምን የምታወሳው ይህች ሥርዓት በላሊበላ በቤተ ማርያም እጅግ ትደምቃለች። እጹብ እጹብም ታሰኛለች።
የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል እና የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የልደት በዓል አዲስ ምዕራፍ ነው፤ የምህረት ዘመን ነው ይላሉ። ይህንም ያስባለው በአባታችን በአዳም፣ በእናታችን በሔዋን ስህተት ምክንያት እግዚአብሔር እና የሰው ልጅ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ተለያይተው ነበረ። እርሱ ግን ከ5 ሺህ 5 መቶ ዘመን በኋላ የተበደለው እግዚአብሔር አብ አንድ ልጁን ወደ በደሉት ልኮ ይቅርታን ስላደረገ ነው።
የልደት በዓልም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም በቤተልሔም ከከብቶች በረት ተወልዶ ፍቅሩን ለሰው ልጆች የገለጸበት ነውና ድንቅ ነው። በዚያን ጊዜ መላእክት ለእግዚአብሔር በሰማያት በአርያም ምስጋና ይገበዋል። በምድርም ሰላም ኾነ እያሉ ዘመሩ።
ስለ ምን ቢሉ የተበደለው እግዚአብሔር ወደ በደሉት የሰው ልጆች በይቅርታ ወርዶ ተወልዷልና። የእርሱስ ይደንቃል፤ እንደ አምላክነቱ አይደለም፤ እንደ ንጉሡ እንደ ዳዊት ቤተሰብነቱ እንኳን በማይመጥነው በከብቶች ግርግም ተወልዷልና። መላእክትን ደነቃቸው፤ የትህትናው ነገር አስገረማቸው።
እግዚአብሔር ዓለሙን እንዲህ ወዶታልና ቁጥራቸው ከምድር አሸዋ፣ ከሰማይ ከዋክብት የላቁት የሰማይ መላእክት ለእግዚአብሔር ዘመሩ። ምስጋና አቀረቡ። እርሱ በተወለደ ጊዜ ዓለም የምትታየውም የማትታየውም ዓለም በምስጋና አረገደች። በዝማሬ ተመላች።
መላእክት ከእግዚአብሔር የሚገኘው እውነተኛው ሰላም ለምድር ይሁን ብለው እንደዘመሩ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ሰላም የተገኘበት፤ ፍቅር የተሰጠበት ነው ይላሉ ብፁዕነታቸው።
ልዑሉ ዝቅ አለ እኛን ከፍ ሊያደርግ፣ ልዑሉ በማይመጥነው በከብቶች በረት ተገኘ። የወደቅነውን ለማንሳት እያልን በፍቅር ፣ በተመስጦ፣ በዝማሬ የጌታችን የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓል እናከብራለን ነው ያሉት።
ሰው በአምላኩ የተደረገለትን እያሰበ ባመሰገነ ቁጥር ከጸጋ ላይ ጸጋ ይጨመርለታል፤ እንዲህም ኾነን ስናከብር በረከተ ሥጋን፣ በረከተ ነፍስን እናገኛለን ነው የሚሉት። ጌታ በተወለደ ጊዜ መላእክት በሰማይ በአርያም፣ እረኞችም በምድር እንደ አመሰገኑት ሁሉ በደብረ ሮሃ በቅዱስ ላሊበላ ቤዛ ኲሉ እየተባለ ይዘመራል።
በቤተ ማርያም በማሜ ጋሪያ ሊቃውንቱ ከላይ ከታች ኾነው ለአምላካቸው ምስጋናን ያቀርባሉ። ውዳሴን ይሰጣሉ ይላሉ ብፁዕነታቸው። የዓለም ሁሉ ቤዛ ዛሬ ተወለደ እያሉ ይዘምራሉ። ከላይ ከጋራው ኾነው የሚዘምሩት የመላእክት ምሳሌ ናቸው። ከታችም ከሥር ያሉት የእረኞች ምሳሌ ይኾናሉ። ይሄም ዝማሬ፣ ይህም የቤዛ ኲሉ ሥርዓት ድንቅ ነው።
እነኾ ዛሬ ሰው እና መላእክት አንድ መንጋ ኾኑ። በእምነት ድምጽ፣ በእምነት ቃል ክርስቶስን ያመሰግኑት ዘንድ አንድ ኾኑ እያሉ ይዘምራሉ ይላሉ ብፁዕነታቸው። ይህም ሥርዓት በቅዱስ ላሊበላ የደመቀ እና የተወደደ ነው። በቤተ ማርያም አምላካቸውን ያለ ድካም ሲያመሰግኑ ያደሩት ሊቃውንት በቤዛ ኲሉ ሥርዓትም ለአምላካቸው ምስጋና አቀረቡ፤ ሰገዱለት። በአንድነት በመንፈሳዊ ድምፅ ዘመሩለት።
ቤዛ ኲሉ ከሩቅም ከቅርብም የሚመጡ የሚደመሙበት፣ ዳግማዊት ቤተልሔምን የሚያዩበት ነው። ሊቃውንቱ ሲያመሰግኑ ምዕምናኑ እልልታውን ያስተጋባሉ። ይህስ ሥርዓት በሰማይ እንጂ በምድር የማይመስል ነው።
መላእክት እንጂ ሰዎች የሚዘምሩበት፣ በአርያም እንጂ በምድር ያለ አይመስልምና።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!