የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በመላው ዓለም እየተከበረ ነው።

41

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሰው እና ፈጣሪ የታረቁበት፣ ፈጣሪ ራሱን ዝቅ በማድረግ ከፍ የማለት ጥበብን ያስተማረበት፣ ታላቅ ኾኖ ሳለ እንደታናናሾቹ ኾኖ ያሳየበትን ይህን ድንቅ ፍቅር በዓለም በተለያዩ አካባቢዎች በተለያየ ሁነት እየተገለጸ ነው።

ኢትዮጵያውያን ከዋዜማው ጀምረው “ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ” እያሉ በማመሥገን ፍቅራቸውን ከዋዜማው ጀምረው ሲገልጹ ቆይተው ወደ ቤት ተመልሰዋል። ሥነ ሥርዓቱ በቤትም ቀጥሎ ያለው ለሌለው እያካፈለ፣ ሀገር አማን ገበያው ጥጋብ ይኾን ዘንድ እየመረቀ በደስታ ይከበራል።

በእርግጥ የክርስቶስን መወለድ ከሁለት ሳምንታት ቀደም ብለው ታሕሣሥ 25 ቀን 2024 ላይ ያከበሩ አሉ። ኤርትራ፣ ግብጽ፣ ሩሲያ፣ ዩክሬን፣ ቤላሩስ፣ ጆርጂያ፣ ካዛኪስታን፣ ሞልዶቫ፣ ሰርቢያ፣ ሞንቴኔግሮ፣ ቡልጋሪያ እና ሜቄዶኒያ ዛሬ የልደትን በዓል እያከበሩ ይገኛሉ።

በዓሉ በሃይማኖታዊ ሥርዓቶች እና እንደየሀገራቱ ባሕል በተለያዩ ክንውኖችም ነው እየተከበረ የሚገኘው፡፡ ኤርትራውያን ከኢትዮጵያውያን ባልተለየ የበዓል ድባብ ነው በዓሉን እያከበሩ ያሉት።

እንዲሁም ሰርቢያውያን እሳት በማቀጣጠል ዙሪያውን ከብበው እራት እየበሉ እና እየጠጡ እያከበሩት ነው።

በጆርጂያውያን ደግሞ በመንገዶች ላይ ሠብሠብ ብለው በመብላት እና በመጠጣት እየተጨዋወቱ በዓሉን እያከበሩት ይገኛሉ፡፡

በዩክሬን የበዓል ድባብ ባለው ግጭት ምክንያት ከወትሮው ቢቀንስም እያከበሩት ነው።

በዓሉ በሩሲያ በ12ቱ ሐዋርያት ተምሳሌትነት 12 ዓይነት ምግቦች ቀርበው እየተመገቡ ቀኑን እያከበሩት ይገኛሉ።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከሰማይ ወደ መሬት፤ ከጣሪያ ወደ መሠረት”
Next articleየአገው ባሕላዊ የገና ጨዋታ በአዲስ አበባ ተካሄደ።