
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ልደቱ ከፈጣሪው ልደት ጋር የተጣጣመለት ቅዱስም ንጉሥም ነው፡፡ በከብቶች በረት ውስጥ የተወለደውን ክርስቶስ ታምኖ የሚያገለግለው ንጉሥ ለበረከት ተጠርቷልና ገና ሲወለድ በንቦች ታጀበ ይሉታል፡፡ የቀዳማዊቷን ኢየሩሳሌም ተስፋ ያጣው አዳም ከፈጣሪው ጋር እርቅ ፈጽሞ የተስፋ ብርሃንን አየባት፡፡
በዳግማዊቷ ኢየሩሳሌም ደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ደግሞ በየዓመቱ ወደ ኢየሩሳሌም በመከራ እና ጭንቅ የሚመላለሱ ክርስቲያኖች ከድካማቸው አርፈው ተፅናኑባት፡፡ በሽታ እና ጦርነት፤ ግጭት እና ሰላም ማጣት በልደት ዳግማዊቷ ኢየሩሳሌም ላሊበላ ለመድረስ ያልገደባቸው ክርስቲያኖችም እንደ ሰባ ሰገል ጽኑዓን ናቸው፤ የሰላም እና የብርሃን ተስፋን አሻግረው የሚመለከቱ፡፡
የኢየሩሳሌምን ጉዞ የቀነሱ፤ እንግልቱን ያስረሱ እነዚያ ጠቢባን እጆች በትውልድ ዘንድ ዘወትር ሲመሠገኑ ይኖራሉ፡፡ ይህ ድንቅ የኪነ ጥበብ ሥራ በጥንታዊቷ ግሪክ፣ በቀደምቷ ኢየሩሳሌምም ኾነ በገናናዋ ሜሶፖታሚያ አልታየም፡፡ ትህትና የገዛቸው እና የእግዚአብሔር ፍቅር ያደረባቸው ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ከትህትናቸው ብዛት “ዳግማዊት ኢየሩሳሌም” እያሉ ይጠሯታል፤ የቀደምቷን ደብረ ሮሃ፤ የአሁኗን ቅድስት ላሊበላ፡፡
ዓለት እንደ ሰው ልጅ የታዘዘላቸው ጠቢባን እጆች ዘመናትን ተሻግሮ ጥንታዊ ሥልጣኔን የሚመሰክር አሻራ ለትውልድ ገጸ በረከት አስቀምጠው አለፉ፡፡ የተፈጥሮን ሕግ እንደ ጅረት ጠብቆ የሚፈስሰው ትውልድም “ዐይኔ ዓለም አየ እግሬ ደርሶ” አለ እንጅ የላሊበላን ኪነ ሕንጻ አምሳያዎች ደግሞ ደጋግሞ ሲታነጽም ኾነ ሲገነባ የማየት ዕድል አላገኘም፡፡ የላሊበላ ኪነ ሕንጻዎች እና ሞት ሁሌም አዲስ ናቸው የሚባለው በምክንያት ይመስላል፡፡
የላሊበላ ኪነ ሕንጻዎችን ጥበብ አይቶ የተረዳ፤ ተመራምሮ የተገለጠለት ማን ይኖራል፡፡ ጎብኝው “ያየሁትን ብናገር ማን ያምነኛል” ያለውም ያለምክንያት አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያውያን ለሃይማኖታቸው ትጉሃን፤ ለሀገራቸው ቀናዒ ናቸውና የወገኖቻቸውን ድካም እና እንግልት ለመቀነስ በፈጣሪ ፈቃድ የሠሯቸው አብያተ ክርስቲያናት ሰማያዊ ተስፋ ምድራዊ በረከት ኾኗቸዋል፡፡
ሰማይ እና መሬት በታረቁበት፤ ፍጡር እና ፈጣሪ በተስማሙበት እና ሰው እና መላዕክት አብረው በዘመሩበት የልደት በዓል ቀን ላሊበላ መገኘት “ከሰማይ ወደ መሬት፤ ከጣሪያ ወደ መሠረት” እውን ይኾናሉ፡፡
የላሊበላ ኪነ ሕንጻዎች የክርስቶስ መወለድ አምሳያዎች ናቸው የሚባለውም ያለምክንያት አይደለም፡፡
በታዘብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!