”የክርስቶስን በዓል ስናከብር ብቻችን አርደን የምንበላ ከኾነ በዓል አይደለም” ሊቀ ጉባዔ ሳሙኤል እንየው

40

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ በድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት ውስጥ አንዱ የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል ነው። በየዓመቱ የሚከበረው ይኼው የልደት በዓል በርካታ ሃይማኖታዊ ይዘቶች እና ታሪኮች ይነገሩበታል። የኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ በትንቢት ተነግረው ለክብሩ ሊሰግዱለት እና ስጦታ ሊያበረክቱ በኮከብ እየተመሩ ወደተወለደበት ቦታ የሄዱት ሰብዓ ሰገል ተጠቃሽ ናቸው።

ሰብዓ ሰገልን እና የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት ምን ያገናኛቸዋል? ኢትዮጵያውያን ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት እና መሰል ሃይማኖታዊ በዓላት ታሪክ ምን መማር አለብን? የሚሉትን ሃሳቦች የሃይማኖቱን ሊቅ አነጋግረናል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ስብከተ ወንጌ ኀላፊ ሊቀ ጉባዔ ሳሙኤል እንየው ስለ ሰብዓ ሰገል እና ተዛማጅ ጉዳዮች ማብራሪያ ሰጥተውናል።

ጀረደሽት የሚባል ፈላስፋ አስቀድሞ የሚኾነውን ትንቢት ሲመለከት ድንግል የኾነች ሴት ሕጻን ታቅፋ በሰሌዳ ኮከብ ላይ ተሥላ በትንቢት በመመልከቱ ይህንኑ ያየውን ነገር በብረት ላይ ሥሎ አስቀመጠው። የሣለውን ሥዕል ትርጉም እና ታሪክም ከመሞቱ በፊት ለሦስት ልጆቹ – ለሰብዓ ሰገሎች በማስረዳት የሚፈጽሙትን ነገራቸው። (በግዕዝ ቋንቋ ሰብዓ ሰገል ማለት የጥበብ ሰዎች ማለት ነው)

የአይሁድ ንጉስ የሚኾን ሰማይ እና ምድርን የሚገዛ ይወለዳል። ይህንን ኮከብ እያያችሁ እጣን፣ ከርቤ እና ወርቅ ወስዳችሁ ስጦታ አቅርቡለት ብሎ ማዘዙን ሊቀ ጉባኤ ሳሙኤል እንየው አብራርተዋል። ከረጅም ጊዜ በኋላም የተነገረለት ኮከብ ሲከሰት ሰብዓ ሰገሎች ከሩቅ ምሥራቅ ተነስተው ኮከቡን በመከተል ወደ ኢየሩሳሌም ቤተልሄም ዋሻ ተጓዙ።

ኢየሩሳሌም ሲደርሱም አዋጅ ነገሩ – ‘የአይሁድ ንጉሳችሁ የት ነው የተወለደው’ ብለው ማፈላለግ ጀመሩ። ‘ሕጻኑ የት ነው የተወለደው’ ብለው እንዳይጠይቁ በኢየሩሳሌም ብዙ ሕጻናት ይወለዳሉና እንዳይፌዝባቸው ሰጉ፤ ‘አምላክ ተወለደ’ ለማለትም በዚያን ጊዜ ሰዎች አምላክ ይወለዳል ብለው አያምኑምና ጥያቄ እንዳይነሳባቸው ስለሰጉ ‘የአይሁድ ንጉሳቸው የተወለደው ወዴት ነው?’ እያሉ በመጠየቅ ኢየሩሳሌም ደረሱ።

የወቅቱ ንጉስ ሔሮድስም በኢየሩሳሌም አግኝቶ ሲጠይቃቸው ፈላስፋ አባታቸው ለሚወለደው የአይሁድ ንጉስ የዓለሙ ሁሉ አዳኝ የነገራቸውን ለመፈጸም እንደኾነ ነገሩት። ሔሮድስም ምድራዊ ተቀናቃኝ ንጉስ መስሎት ሥጋት እንደገባው እና አግኝቶ ለመግደል በልቡ በማሰብ ‘እኔም ሄጄ እንድሰግድለት ከሰገዳችሁ እና ከገበራችሁ በኋላ ስትመለሱ በእኔ በኩል ኑ’ በማለት ሰብዓ ሰገሎችን አዘዘ።

ሰብዓ ሰገሎቹን ከሸኘ በኋላ የአይሁድ ሊቃውንትን ሲያማክር ከድንግል እንደሚወለድ ትንቢት የተነገረለት ክርስቶስ እንደሚኾን ገለጡለት። ከንጉሱ ሔሮድስ ተሰናብተው የወጡትን ሰብዓ ሰገሎች በኮከቡ እየተመሩ ቤተልሔም ዋሻ ደረሱ። ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበትን ዋሻም አገኙ። ኢየሱስም ላንዱ ሕጻን፣ ላንዱ ሽማግሌ እና ላንዱ ወጣት ኾኖ ታያቸው። አባታቸው ከሣለላቸው ሥዕል ላይ ሲመለከቱ ግን ተመሳሳይ ስለኾነላቸው የሄዱለት ንጉስ መኾኑን ተረድተው ወርቅ፣ እጣን እና ከርቤ ገብረውለታል።

የነገሥታት ንጉስ ነህና ወርቅ፣ ካህን ነህና እጣን እንዲሁም የተሰበረውን የምትጠግን ነህና ከርቤ ይገባሃል ብለው እንደገበሩለት የሃይማኖቱ አስተምህሮ እንደሚነግር ሊቀ ጉባዔ ሳሙኤል አብራርተዋል። የተለያየን አንድ የሚያደርገው ከርቤ ተለያይቶ የነበረውን የሰው ልጅ እና እግዚአብሔርን አንድ ታደርጋለህ፤ የተጣሉትን ታስታርቃለህ፤ በአንተ መወለድ አራዊት እና እንስሳት አንድ ኾነው አመስግነዋል፤ ስለዚህ ላንተ ከርቤ ይገባሃል ብለው ስጦታ ማቅረባቸውንም ነው ሊቁ የገለጹት። እጅ ነስተውት፣ ሰግደውለት እና ስጦታቸውን አበርክተው ተመልሰዋልም ብለዋል።

ሰብዓ ሰገሎች ወደ ሀገራቸው ሲመለሱም ሔሮድስ እንዳዘዛቸው እንዳይሄዱ መልዓክ ስላናገራቸው ሔሮድስ እንዳያገኛቸው በተለዋጭ መንገድ መመለሳቸውን ታሪኩ ይነግረናል።

ሲመለሱም ስንቃቸው አልቆባቸው ስለነበር እመቤታችን ቅድሥት ድንግል ማርያም ስንቅ የሚኾን ቂጣ አዘጋጅታ ሰጥታቸዋለች ያሉት ሊቀ ጉባዔ ሳሙኤል እንየው የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ለማክበር በሚደረጉ የተለያዩ ክዋኔዎችም አንዱ አንዱን ማሰብ እና ማክበር፤ በመከባበሩም መደጋገፍ እና መተባበር ሲዘከር እንደሚኖር ገልጸዋል።

አንዱ ለሌኛው ማሰብ እና መጨነቅ የቤተ ክርሥቲያናችን አስተምህሮ ነው፤ ማንኛውም ሰው ክርሥቶስን እያሰበ በዓል ሲያከብር ብቻውን አርዶ የሚበላ እና ተደስቶ የሚውል ከኾነ በዓል አይደለም። የተቸገሩትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስ….ነው እንጂ ሲሉም አስታውሰዋል።

ክርሥቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ወደ ምድር ወርዶ የተወለደው አዳም በሲኦል ወድቆ ስለነበር ከዚያ ለማውጣት ነው። ስለ ሰው ፍቅር ወደዚህ ዓለም መጣ እንዲል መጽሐፉ የሰዎችን ችግር ለመቅረፍ እንደመጣ እና እንደተወለደ ሲታሰብ ክርስቶስ የፍቅር የመተሳሰብ የመረዳዳት እና የአንድነት መገለጫ መኾኑን እናምናለን።

እኛ ሰዎችም ልደቱን ስናከብር አርኣያውን ተከትለን በመተሳሰብ እና በመረዳዳት የተራቡትን በማብላት የተቸገሩትን በመርዳት ከኾነ እውነተኛ የክርስቶስ የልደት በዓል አማኞች እንኾናለን።

ከሃይማኖታዊ ዓላማው እና ሥርዓቱ ውጭ እያረዱ መብላት እና መዋል ክርስቶስን ማሰብ እና ማክበር አይደለም ብለዋል ሊቀ ጉባዔ ሳሙኤል እንየው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሰላም ሰው ሆኖ መገኘት ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት ነው” ብጹዕ አቡነ ሕዝቅዔል
Next article“ከሰማይ ወደ መሬት፤ ከጣሪያ ወደ መሠረት”