“የሰላም ሰው ሆኖ መገኘት ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት ነው” ብጹዕ አቡነ ሕዝቅዔል

29

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የ2017 ዓ.ም የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በቅድስት ላሊበላ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው፡፡ በክብረ በዓሉ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ብፁዓን አባቶች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ካህናት፣ ምዕመናን፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና ጎብኝዎች ተገኝተዋል፡፡

በቅድስት ላሊበላ የልደት በዓል ላይ ተገኝተው ለምዕመኖቻቸው እና ለበዓሉ ተሳታፊዎች ቃለ ቡራኬ የሰጡት የከፋ፣ ሸካ እና ቤንች ማጅ አሕጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የሰዋሰወ ብርሀን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ጠባቂ አቡነ ሕዝቅኤል የመጀመሪያው ልደት በኋለኛው ልደት የተረጋገጠ ኾነ ብለዋል፡፡ ልደቱ ልደታችን፤ መወለዱ ሰላማችን ነው ያሉት ብጹዕነታቸው የቀደመው ልደት ከአብ ያለ እናት የኋለኛው ልደት ደግሞ ከድንግል ያለ አባት የተገኘ ነውና ተስፋ ላጣችው ዓለም ተስፋዋ ኾነ ነው ያሉት፡፡

ልደቱ ሰላምን የሚያበስር ነውና ስለሰላም መጣ ያሉት ብጹዕነታቸው በመምጣቱም የተለያየውን ዓለም አንድ አደረገ ብለዋል፡፡ መለያየት አሁን የመጣ ሳይኾን ቀድሞም የነበረ እንደነበርም አንስተዋል፡፡ ነገር ግን አሉ ብጹዕነታቸው መለያየት ሽማግሌዎች የማይጦሩበት፣ ሕጻናት የማይቦርቁበት፣ የሌላቸው የማይመጸወቱበት ክፉ ነገር ነበርና የአምላክ መወለድ የዓለም ተስፋ ኾነ ነው ያሉት፡፡

ዓምላካችን ስለ እኛ ተወልዷልና ሰላምን እንፈልጋት፤ እንከተላት፤ ማዕዛዋም ያስደስታል ያሉት ብጹዕነታቸው “የሰላም ሰው ኾኖ መገኘት ከእግዚያብሔር ጋር መገናኘት ነው” ብለዋል፡፡ የልደት በዓል ሠሪው እና ተሠሪው፤ ሸማኔው እና ዘሃው የተዋሃዱበት በዓል በመኾኑ እርስ በእርስ ልንዋደድ፣ ልንግባባ እና ልንሰማማ ይገባል ነው ያሉት፡፡

በቅድስት ላሊበላ የሚከበረው በዓል እጥፍ ድርብ በዓል ነው ያሉት ብጹዕነታቸው በጨለማው ዘመን ብርሃን ኾኖ የተገኘው ቅዱስ ላሊበላ ልደቱ ዛሬ ነውና ላሊበላን ዳግማዊት ኢየሩሳሌም ስንል በምክንያት ነው ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የክርስቶስ ልደት የአዲስ ተስፋ ጅማሮ፣ የብሩህ ዘመን ማብሰሪያ እና የሰላም ምልክት ነው” አቶ አራጌ ይመር
Next article”የክርስቶስን በዓል ስናከብር ብቻችን አርደን የምንበላ ከኾነ በዓል አይደለም” ሊቀ ጉባዔ ሳሙኤል እንየው