
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ልደትን በላሊበላ እጅግ ደማቅ እና ሁሉም ሊያየው የሚጓጓለት ሁነት ነው። የ2017 ዓ.ም የልደትን በዓል በላሊበላ መርሐ ግብርም ከአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት የተሠባሠቡ አማኞች እንዲሁም ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ጎብኝዎች በተገኙበት በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
በበዓሉ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በኢትዮጵያ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት ውስጥ አንዱ ነው ብለዋል። ልደት በሃይማኖቱ አስተምህሮት ሥርዓት እና ትውፊት መሠረት ከሚከበርባቸው ሥፍራዎች መካከል የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን ቀዳሚው ነው ብለዋል።
በዓሉ ድርብ በዓል ነው፤ ዕለቱ የኢየሱስ ክርስቶስ እና የቅዱስ ንጉሥ ላሊበላ የልደታቸው በዓል ታስቦበት የሚውል ነው ብለዋል ዋና አሥተዳዳሪው። ይህም በዓሉን እጥፍ እና ድርብ ድምቀት ይሰጠዋል ነው ያሉት። የክርስቶስ ልደት የአዲስ ተስፋ ጅማሮ፣ የብሩህ ዘመን ማብሰሪያ እና የሰላም ምልክት ስለመኾኑም ተናግረዋል። ልደት ጨለማ እና የሞት ጥላ ተሽረው ብሩህ ጮራ የፈነጠቀበት ነጻነት፣ ፍቅር እና የሰው ልጆች ሰላም የተገኘበት አዲስ ምዕራፍ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ያገኘነው ሰላም፣ ነጻነት እና ፍቅር ለኛ የተከፈለ ዋጋ በመኾኑ ሁላችንም ይሄንን በመረዳት ጥላቻን በፍቅር ቀይረን ለቀጣዩ ትውልድ ሰላሟ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ልናስረክብ ይገባል ነው ያሉት። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ የታየው የሰላም እጦት ሕዝብን እየፈተነ ቆይቷል፣ ዛሬ ላይ ግን ሰላሙ ተመልሶ ልደትን በላሊበላ በሰላም እየተከበረ ነው ብለዋል። በልደት ያገኘነውን ሰላም በዘላቂነት ለማጽናት ሁላችንም በአንድነት መቆም ይገባናል ሲሉም አሳስበዋል።
የቤዛ ኩሉ ሥርዓት በቅርብ እና በሩቅም ለሚያዩት ሁሉ መንፈስን የሚያድስ፣ የላሊበላ ኪነ ሕንጻም ዘመን ተሻገሪ የኾነ ድንቅ ጥበብ ነው ብለዋል። በዓለም መዝገብ ውስጥ ስሙ በሰፈረው ቅርስ ውስጥ ሃይማኖቱ ሥርዓቱን ጠብቆ እንዲተላለፍ ለሚያደርጉት የአካባቢው ነዋሪዎችም ምሥጋና አቅርበዋል።
ዋና አስተዳዳሪው በመልዕክታቸው “እንግዳ ተቀባዩ እና ሁልጊዜም ለሰላም ለሚተጋው ለላሊበላ እና ለመላው ላስታ ሕዝብ ምሥጋና እና አክብሮቴን እገልጻለሁ” ነው ያሉት። ዋና አሥተዳዳሪው ይህ ታላቅ በዓል ከሃይማኖትነት ባሻገር ባሕላዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የላቀ ነው፤ ለሀገር ገጽታ ግንባታም ከፍተኛ ፋይዳ አለው ብለዋል።
በሰላም እጦት ችግር ምክንያት የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንደገና በማንቀሳቀስ ረገድ ሁላችንም ለሰላም ዘብ መቆም አለብን ሲሉም አስገንዝበዋል። ሰላምን በመጠበቅ በሰሜን ወሎ ዞን ብሎም በአማራ ክልል ያለውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ የበለጠ ማሳደግ፤ ዜጎችንም ከቱሩፋቱ ተጠቃሚ ማድረግም ለነገ የማይባል ሥራ መኾኑን አመላክተዋል።
“በዓሉን ስናከብር የሁሉም ነገራችን መሠረት የኾነውን ሰላማችንን በመጠበቅ እና የተቸገሩትን በመርዳት መኾን አለበት” ሲሉም ተናግረዋል። በዓሉ በሰላም እና በደመቀ ሁኔታ እንዲከበር ላስቻሉ የጸጥታ አካላት እና መላው የበዓሉ አስተባባሪዎችም ምሥጋና አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!