“እርቅ የቂም እና የጥላቻ ማፍረሻ ዓቅም ነው” አፈ ጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ

32

ባሕር ዳር ታኅሣሥ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ገዳማት በድምቀት እየተከበረ ነው። በበዓሉ የታደሙት የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ መልዕክት አስተላልፈዋል። በመልዕክታቸው ለመላው ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንኳን አደረሣችሁ ብለዋል። የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አረጋ ከበደን የእንኳን አደረሣችሁ መልዕክትም ተወክለው አስተላልፈዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በመወለዱ አልጫ የነበረውን ዓለም ሕይወት ዘራበት፤ በመወለዱም የአዲስ ምዕራፍ መጀመሪያ ኾነ ብለዋል። የጠቡም ግድግዳ የፈረሰ እና የእርቅም ምልክት እንደኾነ ገልጸዋል። የሰው ልጆችም ትዕዛዝን በመተላለፍ የልጅነት ክብሩን አጥተው ወደ ሲኦል ሲወርዱ ሰውን ለማዳን ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ዓለምን እንዳዳነ የሃይማኖት አባቶች አጥብቀው ያስተምራሉ ነው ያሉት።

“እርቅ የቂም እና የጥላቻ ማፍረሻ አቅም እንደኾነም” ገልጸዋል። በሀገራችን ያጋጠመው የሰላም መደፍረስ እና የእርስ በርስ ግጭት ሊቆም ይገባል ነው ያሉት። ባለፈው ዓመትም በጦርነት ተሞክሮ የተፈታ ችግር አለኖሩንም ጠቅሰዋል። ይልቁንም የእርስ በርስ ግንኙነትን እና ወንድማማችነትን የበለጠ ማሻከሩንም ተናግረዋል።

ቅሬታ ያለው ግለሰብም ሆነ ቡድን በተጀመረው አግባብ ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት ራሱን ዝግጁ ማድረግ ይጠበቅበታል ነው ያሉት። ጦርነት እጅግ መራራ እና አስከፊ መኾኑን በተግባር ያየነው እውነት ነው። አሁንም ጦርነት ሰላም ስለማያመጣ ሁሉም አካል እጁን ለሰላም እንዲዘረጋ ምዕመኑ እና የሃይማኖት አባቶች ተጽዕኖ ማሳደር እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ጥላቻ እንዲወገድ እና ሰላም እንዲሰፍን የላሊበላ እና አካባቢው ሕዝብም እውነት ላይ ቆሞ መመካከር እና አጥብቆ መወያየት ያስፈልገዋል ብለዋል። የላሊበላ ከተማ የኢትዮጵያ ብቻ ሳትኾን የመላው ዓለም ሕዝቦች ከተማ ናት ብለዋል። በተለይም የከተማው እና የአካባቢው ሕዝብ የሚተዳደርበትን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ እንዲያንሰራራ ለሰላም የሚያስፈልገውን ምክክር ያለምንም መሸፋፈን እና መደባበቅ በእውነት ላይ ቆሞ አስፈላጊውን ምርጫ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል። ጦርነትን የሚቀሰቅስ አካልንም ወደ ውይይት እንዲመጣ በማድረግ የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጠይቀዋል።

የአማራ ክልልም ኾነ የፌዴራሉ መንግሥት በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ እያቀረበ ነው። ዛሬም ቢኾን መንግሥት በማንኛውም ጊዜ ለሰላም በሩ ክፍት መኾኑን አረጋግጠዋል።

በዓሉን ስናከብር አቅመ ደካማ ወገኖችን በመደገፍ እና ሃይማኖታዊ አስተምህሮውን በመተግበር በመረዳዳት መኾን እንዳለበትም አፈ ጉባኤዋ አሳስበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የላሊበላ አካባቢ ቅርሶችን የመንከባከብ ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል” ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ
Next article“የክርስቶስ ልደት የአዲስ ተስፋ ጅማሮ፣ የብሩህ ዘመን ማብሰሪያ እና የሰላም ምልክት ነው” አቶ አራጌ ይመር