
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ለማክበር በላሊበላ ተገኝተው የእንኳን አደረሳቹህ መልዕክት አስተላልፈዋል። ኢትዮጵያ በርካታ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት መኾኗንም ገልጸዋል። ሀገሪቱ ያላትን ቅርስ በዩኔስኮ በማስመዝገብ በአፍሪካ ግንባር ቀደም እንድትኾን አድርጓታል ብለዋል።
ከእነዚህ ቅርሶች ውስጥ ደግሞ የዓለማችን የኪነ ሕንጻ ጥበብ የታየባቸው እና ዩኔስኮም በድንቅነታቸው የመዘገባቸው የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አንዱ መኾኑን ገልጸዋል። ቅርሶቹ ሀገሪቱም ለዓለም ካበረከተቻቸው ዘመን አይሽሬ ቅርሶች መካከል ከቀዳሚዎች ተርታ የሚመደቡ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ቅዱስ ንጉሥ ላሊበላ ጥለውት ያለፉትን የዓለም ቅርስ ለመጭው ትውልድም ለማስተላለፍ መንግሥት የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን እና ድልድዮችን መሥራቱን ገልጸዋል። የመታጠቢያ ቤት ግንባታ፣ ማኅበራትን የመደገፍ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። በቀጣይም የላሊበላ አካባቢ ቅርሶችን የመንከባከብ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንደ ሀገር ከቱሪዝም ዘርፉ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ የቱሪስት አገልግሎት ሰጭዎች ቁጥር እንዲጨምር እና የቱሪዝም ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
በቱሪዝሙ ዘርፍ ከአፍሪካ ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ ነባር መዳረሻዎችን ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን ባሟላ መንገድ ከማልማት ባለፈ አዳዲስ መዳረሻዎችንም በማስፋፋት የሀገሪቱን መልካም ገጽታ የመገንባት ሥራ እየተሠራ ነው፤ ማኅበረሰቡንም ከዘርፉ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል። ለዚህ ደግሞ የጎርጎራ መዳረሻ እና የባሕር ዳር አካባቢ መዳረሻዎችን ለአብነት አንስተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!