
ወልድያ: ታኅሣሥ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ)እንዲህ ያለ ሥርዓት አይታችኋልን? አንዲህ ያለ ዜማ አድምጣችኋልን? እንዲህ ያለ ረቂቅ ነገር ተመልክታችኋልን? እኒያን ጥበባት ያዩ የተባረኩ ናቸው። እኒያን ድምጾች የሰሙ ጀሮዎችም የታደሉ ናቸው። በቅዱሳኑ ሥፍራም የተመላለሱ ዕድለኞች ናቸው።
ሰማይን በመሰለች፣ በረቀቀ ጥበብ በተሠራች ቅድስት ሥፍራ የኾነው ሁሉ ይደንቃል። ያን የመሰለ ሥርዓት አይቶ የማይደንቀው ይገኛልን? ያን የመሠለ ትህትና ተመልክቶ አጀብ የማይል ይኖራልን? ዲያቆናቱ ያለ ማቋረጥ ለአገልግሎት ይፋጠናሉ። ሊቃውንቱ ስብሐተ እግዚአብሔርን ያደርሳሉ። ጳጳሳቱ ከዳር እስከ ዳር የሞላውን ሕዝብ ይባርካሉ። አማኞች ለአምላካቸው እልልታን ያቀርባሉ። በእጃቸው እያጨበጨቡ ምሥጋናን ይሰጣሉ።
ሮሃ በዝማሬ ተመላች፣ በምስጋና ተከበበች፣ የቅዱሳኑ ከተማ በእልልታ ተዋጠች፣ ለምሥጋና በተዘረጉ እጆች ተጨነቀች። ጳጳሳቱ፣ ሊቃውንቱ፣ ዲያቆናቱ፣ ቀሳውስቱ እና መነኮሳቱ ልብን በምታቀልጥ ዜማቸው፣ ቀልብን በምትገዛ ሥርዓታቸው ዘመሩ። በጥንቷ ሮሃ በአሁኗ ላሊበላ ሰማይ ሥር ጨለማ ተረሳች። ሌሊትም ቀን ኾነች። የጌታ ልደት ነውና ምድር ብርሃን እንደሰጠች አደረች። ሮሃ በውዳሴ፣ በቅዳሴ አነጋች።
በልብሰ ተክህኖ የተዋቡት ሊቃውንት፣ መቀመጥ ሳያምራቸው፣ ድካም ሳይረታቸው፣ ረሃብና ጥም ሳያሸንፋቸው ከማዕልት እስከ ሌሊት በደጀ ሰላሙ ተመላለሱ። በጽናት ቆመው ከሰማየ ሰማያት ለወረደው፣ ከድንግል ማርያም በከብቶች በረት ለተወለደው ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሥጋና አቀረቡለት። ክብር ለአንተ ይሁን አሉት።
ምድር ዘመረች፣ ሰማይም አዜመች። ላሊበላም ጨለማን ረስታ አደረች። ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በቅድስቷ ከተማ ላሊበላ የተገኙ ሌሊቱን በእልልታ ጀምረው በእልልታ ጨረሱት። በዝማሬ ጀምረው በዝማሬ ፈጸሙት።
ደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በታላቅ ሥርዓት የሚከበርባት ናትና ከኢትዮጵያ ከአራቱም አቅጣጫ የሚመጡ አማኞች ይሠባሠቡባታል። ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኙ እንግዶችም በላሊበላ ይገኛሉ። ከኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ጋር የባለሟሉ የቅዱስ ላሊበላ ልደትም ይከበራል።
አስቀድሞ ገና በላሊበላ ተገኝቶ የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ያከበረ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ጌታ በተወለደባት በቤተልሔም እንደተገኘ ይቆጠርለታል ተብሎ ቃል ኪዳን እንደተሰጠ የበረከት ተከፋይ ለመኾን የሚሹ አማኞች ሁሉ በአብያተክርስቲያናቱ አጸድ ሥር በኅብረት እና በአንድነት ይቆማሉ። በበረት ተወልዶ ከወደቁበት ላነሳቸው ጌታቸው እና መድኃኒታቸው ምሥጋና ያቀርባሉ።
የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ለማክበር ላሊበላ የተገኙ አማኞችም በቤተ ማርያም ዙሪያ በኅብረት ኾነው ዘር ሳይቀድመው፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም በድንግልና ተጸንሶ፣ በድንግልና የተወለደውን የኢየሱስ ክርስቶስን የመወለዱን ብሥራት በእልልታ እና በዝማሬ ሲገልጹ አደሩ።
ቤተ ማርያም በልጆቿ፣ በአገልጋዮቿ ተከባ አደረች። በዝማሬ አነጋች። በዙሪያዋ ያደረው ዝማሬ እና ምሥጋና የሚደንቅ ነው። በቤተልሔም በተወለደ ጊዜ ሰው እና መላእክት እንዳመሠገኑት በቤተ ማርያምም ዲያቆናት እና ቀሳውስት፣ መነኮሳት እና ጳጳሳት፣ ደናግላን እና መዘምራን፣ አንባቢያን ሁሉ በኅብረት ሲያመሠግኑት አደሩ።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!