
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ የልደት በዓልን አስመልክተው የመልካም ምኞት መግለጫ አስተላልፈዋል። በዓሉ እንደወትሮው ሁሉ በሰላም እና በፍቅር እንዲጠናቀቅ የሚያስችሉ ዝግጅቶች ስለመደረጋቸውም አብራርተዋል።
የልደት በዓል በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች እና በመላ ሀገሪቱም በድምቀት የሚከበር ሃይማኖታዊ በዓል መኾኑን በመግለጫቸው አንስተዋል። በዓሉ በአማራ ክልል በተለይም በላሊበላ በልዩ ኹኔታ እንደሚከበር ተናግረዋል። በዓሉ ሃይማኖታዊ በዓል ነው፤ የደስታም ምንጭ ነው፤ ሕዝቡም ፈጣሪውን በመለመን እና ማኅበራዊ መስተጋብሩን በማጠናከር ያከብረዋል ነው ያሉት።
ልደት በላሊበላ ከአካባቢው እና ከክልሉ ነዋሪዎች በተጨማሪ መላ ኢትዮጵያውያን እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎችም በቦታው እየተገኙ የሚያከብሩት በልዩ ልዩ ኹነቶች የታጀበ ስለመኾኑ ርእሠ መሥተዳደሩ አንስተዋል።
በበዓሉ በርካታ እንግዶች ይታደማሉ፤ እንግዶች በሰላም መጥተው እና በዓሉን ታድመው በሰላም እንዲመለሱ ለማስቻል በቂ ዝግጅት ሲደረግ ስለመቆየቱም ተናግረዋል።
ርዕሰ መሥተዳደሩ በዓሉን ለማክበር ከመንግሥት የሚጠበቁ ሁሉም ዓይነት ዝግጅቶች ተደርጓል ብለዋል። በዓሉ ሃይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ፣ ሰላሙ ተረጋግጦ እና ለቱሪስቶችም ሃሴትን በሚፈጥር መልኩ እንዲከበር የሚያስችል አደረጃጀት ተፈጥሮ ወደ ቦታው በመጓዝ የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውን ስለመቆየቱም ተናግረዋል።
ርእሰ መሥተዳደሩ “ልደትን በላሊበላ መላው ኢትዮጵያውያን እና በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ በቦታው ለመገኘት የሚጓጉለት በዓል ነው” ሲሉም ገልጸዋል።
በመኾኑም በዓሉን ከማድመቅ በተጨማሪ የመብራት፣ የቴሌ እና ተያያዥ አገልግሎቶች እንዳይቆራረጡ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል። በዓሉን በአካል ተገኝተው መከታተል ያልቻሉ እና በሩቅ ኾነው ለሚናፍቁ ሁሉ ሙሉ ኹነቱን በሚዲያ ተደራሽ ለማድረግ የተቀናጀ የመገናኛ ብዙኃን ስምሪት ስለመሰጠቱም ርእሰ መሥተዳደሩ ገልጸዋል።
አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽንም እንደተለመደው በሁሉም የዘገባ አማራጮች በዓሉን በቀጥታ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ተከታታዮቹ የሚያደርስ ይኾናል።
በልደት በዓል በሁሉም የክልሉ አካባቢ በሰላም እንዲጠናቀቅ ሕዝቡ ዋነኛ የሰላሙ ጠባቂ መኾን እንደሚገባውም ርእሰ መሥተዳደሩ አሳስበዋል።
ሕዝቡ አካባቢውን በንቃት እየተከታተለ ጸጥታውን በማስከበር በዓሉን በእፎይታ ማሳለፍ አለበት፤ መንግሥት ደግሞ ሕዝቡን በማደራጀት እና በማወያየት ከሕዝብ አቅም በላይ የኾኑ ችግሮችንም በመፍታት ኀላፊነቱን ይወጣል ብለዋል።
ልደት ታላቅ ሃይማኖታዊ የሕዝብ በዓል ነው፤ በዓል እና ፖለቲካ አይገናኝም፤ በዓሉ በሰላም እንዳይውል እና ሕዝቡም እረፍት እንዲያጣ በማድረግ የፓለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚያልሙ አካላት ካሉም ቆም ብለው ማሰብ እንዳለባቸውም መልእክት አስተላልፈዋል።
እንዲህ አይነት አጉል የፓለቲካ ትርፍ የሚያልሙ አካሄዶች እንዳይኖሩም በቂ ሰላም የማስከበር ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል የሰላም ኹኔታ እጅግ እየተሻሻለ መምጣቱን የጠቆሙት ርእሰ መሥተዳደሩ በመንግሥት እና በሕዝቡ ቅንጅት የ2017 ዓ.ም የልደት በዓል በሁሉም አካባቢዎች ያለምንም የጸጥታ ስጋት ተከብሮ እንደሚውል አረጋግጠዋል።
ርእሰ መሥተዳደሩ በዓሉን ለሚያከብሩ መላው የአማራ ክልል ሕዝብ እና ለኢትዮጵያውያን በሙሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአብሮነት እና የመተሳሰብ እንዲኾን መልዕክት አስተላልፈዋል።
በዓሉን አያይዘው ባስተላለፉት የመልካም ምኞት መግለጫ “እኛ ኢትዮጵያውያን አብረን ስንኾን እና ስንመካከር ነው የሚያምርብን፤ በጋራ በመሥራት ከድህነት መውጣት እና የተሻለ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ መቀመጥ አለብን፤ የሀገራችን ስም ከድህነት ጋር ተያይዞ መጠራቱ ማክተም አለበት” ብለዋል።
ለዚህም የሀገራችንን ጸጋዎች በሙሉ አሟጠን በመጠቀም ሁሉንም ሕዝቦች እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ ኢኮኖሚ ለመገንባት ሳንታክት እንሠራለን ነው ያሉት።
ሀገራችን ዕውቀትና ምግባርን አዋህዶ የያዘ፣ በቴክኖሎጂም ብቁ የኾነ ማኅበረሰብ ያስፈልጋታል፤ ሰላም የሰፈነበት እና የሕግ የበላይነት የተረጋገጠበት፣ ከዜጎቿም አልፋ ለጎረቤቶቿ የተመቸች፣ በዓለም አደባባይም ተደማጭ የኾነች ሀገር መገንባት አለብን ብለዋል።
አማራ ክልል ትልቅ ክልል ነው፤ የክልሉ ሕዝብም እንደትልቅነቱ የበለጸገች ኢትዮጵያን ዕውን በማድረጉ ረገድ አስፈላጊውን ሁሉ አወንታዊ አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት፤ እንደሚያደርግም እተማመናለሁ ሲሉ ገልጸዋል ርእሰ መሥተዳደሩ በበዓል መልዕክታቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!