
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ምዕራብ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ዋና ጸሐፊ መጋቢ ገብሬ አሰፋ ለልደት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
መጋቢ ገብሬ አሰፋ በመላው ዓለም ለሚኖሩ ለሁሉም የሰው ልጆች እንዲሁም በተለያዩ ኹኔታዎች ውስጥ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንኳን ለ2017ኛው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ ብለዋል።
እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን ታላቅ ፍቅር የገለጠበት፤ አንድ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደዚህ ዓለም በመላክ በሰው አምሳል የሰው ሥጋ ለብሶ እንዲገለጥ፤ በሰዎች መካከል እንዲታይ፤ ከውልደቱም በረት ውስጥ እንዲገኝ ያደረገበትን ምስጢር ስንመለከት እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን ታላቅ ፍቅር የሚያሳይ እንደኾነም አሰረድተዋል።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በውልደቱ የጀመረው ትህትና እና ለመስቀልም ሞት ራሱን አሳልፎ የሰጠበት ምስጢሩ የሚነግረን እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ምን ያህል እንደወደደ ነው ብለዋል።
በራሱ ሐጢያት ምክንያት ከገነት የተባረረውን ሰው እግዚአብሔር መልሶ ከራሱ ጋር ያስታረቀበትን እና የራሱ ያደረገበትን ኹኔታ ስንመለከት አስደናቂ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
ይህ የልደት ቀን በታላቁ መጽሐፍ ለሕዝብ ኹሉ የሚኾን ታላቅ ደስታ እነግራችኋለሁ ብሏልና በችግር እና በተለያዩ ኹኔታዎች ለነበሩ ሰዎች ታላቅ የምሥራች ነው፤ ሁላችንም የምሥራቹ ተካፋዮች ነን ነው ያሉት።
ልደቱን የሚያከብር ሁሉ ኢየሱስ ለሰው ልጅ ያሳየውን ፍቅር በማስተዋል ከሱ በመማር ፍቅርን መለማመድ እና የእሱን ፍቅር ለሌሎች ማሳየት እንደሚገባም ገልጸዋል።
ክርስቲያኖች በዚህ ታላቅ በዓል ለአቅመ ደካሞች ያላቸውን በማካፈል እና በመርዳት በዓሉን እንዲያሳልፉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ክፋትን፣ ተንኮልን፣ ሴራን፣ ምቀኝነትን፣ አመጽን እና መገዳደልን ማስወገድ እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገር የተናገሩት መጋቢ ገብሬ አሰፋ እንደዚህ ዓይነት የሐጢዓት ልምምዶችን በማስወገድ መኖር እንደሚገባም አሳስበዋል።
እርስ በእርስ በመፈቃቀር እና የሰላም አምባሳደር በመኾን ሕዝብን ማገልገል ይገባልም ነው ያሉት።
መጋቢ ገብሬ አሰፋ በዓሉ የሰላም፣ የደስታ፣ የፍቅር እና የትህትና እንዲኾንም ተመኝተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!