
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 28/2017 ዓ.ም(አሚኮ)በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር እና ደሴ ካቶሊካዊ ሰበካ ጳጳስ አቡነ ልሳነ ክርስቶስ ማቲዮስ ለልደት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።
አቡነ ልሳነ ክርስቶስ ማቲዮስ በመልዕክታቸው የተከበራችሁ የሀገረ ስብከታችን ካቶሊካውያን ምዕመናን፣ ካሕናት፣ መነኮሳት እና መነኮሳን እንዲሁም መልካም ፈቃድ ያላችሁ የክልላችን ሕዝቦች፣ በሀገርም ኾነ ከሀገር ውጪ የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ሁሉ እንኳን ለ2017 ዓ.ም የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደት አደረሳችሁ ብለዋል።
“የልደት በዓል የእግዚአብሔርን ፍጹም ፍቅር ያየንበት፣ የመዳናችን ተስፋ የተገለጠበት ትልቅ የደስታ ቀን ነው” ያሉት አቡነ ልሳነ ክርስቶስ ማቲዮስ ከሞት ዕዳ ነጻ የሚያወጣው እስኪመጣ ድረስ በጭንቅ የቆየው የሰው ዘር መልካም ዜናን ሰማ ነው ያሉት።
በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የእዳ ደብዳቤያችን መሰረዝ ተስፋችን ተረጋገጠ ያሉት አቡነ ልሳነ ክርስቶስ ማቲዮስ ይህ ተስፋ ባለፉት ዘመናት ለነበሩት ብቻ ሳይኾን ዛሬም በግል፣ በቡድን፣ በማኅበርም ምክንያት በውጥረት፣ በስጋት እንዲሁም በጭንቀት ውስጥ ለምንገኝ ለዛሬው ትውልድም አስተማማኝ ተስፋ ነው ብለዋል።
በዓሉ አምላክ ኾኖ ሳለ ሰው ስለኾነው በዚህ በልደት ቀን የተፈጸመውን ታላቅ የደኅንነት ምስጢር ስለያዘው ሕጻን የተነገረበት ጊዜ ነበር ነው ያሉት።
እረኞች የጌታን መወለድ ምሥራች በሰሙ ጊዜ ከሰማይ መላዕክት ጋር ኾነው ዘመሩ ያሉት አቡነ ልሳነ ክርስቶስ ማቲዮስ መልዕክቱም በሰማይ እና በዙፋኑ ለተቀመጠው የሚገባውን ክብር ሲደርሰው በእርግጥም በምላሹ ደግሞ ሰላምም በምድር በትጋት ለሚጠብቁት ሁሉ እንደሚደርስ ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
ዛሬም የሰው ልጅ ከሰላም የበለጠ የሚፈልገው እና ቢያገኘውም ሊደሰትበት የሚችል ነገር የለም። ይህ የሰላም ጉዳይ ሁሉም በጋራ ከእንቅልፉ መንቃትን እና መተባበር፤ ከጥፋት መመለስን እና ሰላም ማውረድን፤ በእውነተኝነት በጋራ መሻትን የሚጠይቅ ጉዳይ እንደኾነ ገልጸዋል።
የሰላማችን መምጣት በሰላም እጦት ተጨንቀን የምንገኝ ሁሉ ትኩረታችንን ሊስብ ይገባል። ስለዚህ የሚገባውን ክብር ለአምላካችን ልንሰጥ ተጠርተናልና ሳንቆጥብ እንድንሰጠው ይገባናል ብለዋል።
የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ስናከብር በዙሪያችን የሚገኙትን ችግረኞችን እናስባቸው ብለዋል። የጦርነት ሰለባ የኾኑትን የክልላችን እና የሌሎችንም ክልሎች ሰዎች እናስባቸውም ብለዋል።
በማረሚያ ቤት፣ በሆስፒታል፣ በድንበር ጥበቃ ላይ ለምትገኙ ሁሉ እግዚአብሔር እንኳን ለ2017 ዓ.ም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በሰላም በጤና አደረሳችሁ ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን