
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ ለመሥራት የሚያስችሉ ተግባራት ላይ መልዕክት ተላልፈዋል። የቀያሽ አርሶ አደሮች እና የመሥሪያ መሳሪያ ልየታ፣ የተፋሰስ ካርታ ሥራ እና የአፈር እና ውኃ እቀባ ተግባራትን የመለየት ሥራ መከናወኑን በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ገልጸዋል።
በ2017 ዓ.ም ከዘጠኝ ሺህ በላይ ተፋሰሶች ላይ ከ366 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የተለያዩ የአፈር እና ውኃ ዕቀባ ሥራዎች እንደሚሠሩ ነው የገለጹት። ከዚህ በፊት የተሠራን ከ150 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ደረጃቸውን የማስጠበቅ ሥራ ይከወናልም ብለዋል። በልማት ሥራው ላይ ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የሰው ሃይል ይሳተፋል ነው ያሉት።
እስከ ጥር 15/2017 ዓ.ም ባለው ጊዜ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በማጠናቀቅ የሙከራ ሥራ የሚጀመር ይኾናል ብለዋል። ከጥር 15/2017 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በክልሉ መደበኛ ሥራው በንቅናቄ ይከናወናል ነው ያሉት። በበጋ የተሠራውን የአፈር እና ውኃ እቀባ ሥራ በሥነ ሕይወታዊ ዘዴ ለማጠናከር ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን በላይ የተለያዩ የዕፅዋት ችግኞችን የማዘጋጀት ሥራ እየተሠራም ነው።
ኀላፊው እስከ አሁን በክልሉ በተሠራው የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ ውኃማ አካላት እንዲጎለብቱ እና የተጋለጡ ተራሮችም በደን እንዲሸፈኑ እያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል። የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎች ተቋማትም ጥናት ማድረጋቸውን የገለጹት ኀላፊው የተፈጥሮ ሐብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ በአግባቡ በተሠራባቸው አካባቢዎች እስከ 72 በመቶ የምርት ጭማሪ ማሳየቱን ጥናቱ አሳይቷል ብለዋል።
በቅርቡ የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት ያጠናውን ጥናት መሠረት አድርገው ደግሞ “ከዚህ በፊት የተሠራው የተፈጥሮ ሃብት ሥራ ምርታማነትን መጨመር ላይ ለውጥ አሳይቷል” ነው ያሉት። የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የልማት ዘላቂነት ለማስቀጠል ማኅበረሰባዊ ተሳትፎን ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።
ባለፉት ዓመታት እየተከናወነ የመጣውን የተፈጥሮ ሃብት ሥራ ይበልጥ ለማጎልበት በቀጣይም ማኅበረሰቡን ባሳተፈ መንገድ መሥራት እንደሚገባ ነው የተናገሩት። ከተፈጥሮ ሃብት ሥራው ባለፈ የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን በአግባቡ መምራት ይገባል ብለዋል።
በክልሉ የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች እና የመብራት መሠረተ ልማቶች ተጠናቀው አገልግሎት እንዲሠጡ ተቋማት ኀላፊነት ወስደው እንዲሠሩም አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!