
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አሥኪያጅ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣ የባሕር ዳር እና ሰሜን ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አብርሐም ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ብጹዕነታቸው በእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ሰማይ እና መሬት፤ ፈጣሪ እና ፍጡር እርቅ የፈፀሙበት ነውና በክርስቲያኖች ዘንድ የተለየ ትርጉም አለው ብለዋል።
በዓሉን የምናከብር ክርስቲያኖች ክርስቶስን በመምሰል እና ክርስቲያናዊ ተግባራትን በመፈጸም ሊኾን ይገባልም ነው ያሉት።
በዓሉ የሰውን ልጅ ፍለጋ ዋጋ ሊከፍል የመጣውን ክርስቶስ ኢየሱስ የምናስብበት እና የምንሠባሠብበት ነው ያሉት ብጹዕነታቸው “ልደቱ ልደታችን ነውና በመተሳሰብ እና በፍቅር እናሳልፈዋለን” ብለዋል።
የተወለደው ኢየሱስ የሰላም አባት በመኾኑ ለምድር ሰላም እና እርቅ ክርስቲያኖች የበኩላችን ሁሉ ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
በበዓሉ መተሳሰብ እና መረዳዳት እንደሚገባም አባታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!