“ላሊበላ የኢትዮጵያውያንን ጥበብ፣ ራዕይ እና ጥንካሬ ያሳየ ድንቅ ስፍራ ነው” ሰላማዊት ካሳ

9

ወልድያ: ታኅሣሥ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ለማክበር ላሊበላ የገቡት የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የላሊበላ አብያተክርስቲያናትን ጎብኝተዋል። ሚኒስትሯ በአብያተ ክርስቲያናቱ እየተገነቡ ያሉ የጥገና እና የመዳረሻ ልማት ሥራዎችንም አይተዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ በላሊበላ የሚያስደስት እና የሚያስደንቅ ነው ብለዋል። የጥገና ሂደቱን መመልከታቸውን ነው የተናገሩት። ሥራዎቹ በጥሩ ኹኔታ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ሁለተኛውን ዙር የጥገና ሥራ ለማስጀመር ከፈረንሳይ መንግሥት ጋር መፈራረማቸውን አመላክተዋል። በሥራው የሀገር ውስጥ ባለሙያዎች እየተሳተፉበት መኾኑን ነው ያመላከቱት። ሥራዎቹ የቱሪዝም ፍሰትን የመጨመር አቅም እንዳላቸውም ገልጸዋል።

በዓለም ላይ በሃይማኖት ቱሪዝም በሚሊዮን የሚቆጠሩ እንግዶች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እንደሚመላለሱ የተናገሩት ሚኒስትሯ የላሊበላ አብያተክርስቲያናትም ብዙ የሃይማኖት ተጓዦችን እንደሚስብም ገልጸዋል። የላሊበላ አብያተክርስቲያናት ከሃይማኖት ተጓዦች ባለፈ ሌሎች እንግዶችም መዳረሻ እንደሚያደርጉት ተናግረዋል።

የኪነ ሕንጻ ባለሙያዎች የላሊበላ ድንቅ አብያተክርስቲያናትን ማየት እንደሚፈልጉም ገልጸዋል። ላሊበላ የኢትዮጵያውያንን ጥበብ፣ ራዕይ እና ጥንካሬ ያሳየ ነው ብለዋል። የላሊበላ አብያተክርስቲያናትን መጎብኘት የብዙ አማኞች ሕልም መኾኑንም አንስተዋል።

የላሊበላ አብያተክርስቲያናት የቱሪዝም ፍሰት እንዲጨምሩ የአካባቢውን ሰላም ማስጠበቅ ይገባልም ብለዋል። ከቱሪዝም ፍሰቱ ጋር ተያይዞ ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ ቋሚ ለማድረግ ሰላም እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

መንግሥት ድንቅ ለኾኑት አብያተክርስቲያናት ትኩረት መስጠቱንም ተናግረዋል። በላሊበላ አብያተክርስቲያናት ብዙ ሥራዎች እንደሚጠበቅ የተናገሩት ሚኒስትሯ በሁለተኛው ዙር የጥገና ሥራ ብዙ ሥራዎች እንደሚከወኑ ነው ያመላከቱት።

የላሊበላ አብያተክርስቲያናትን ብቻ ሳይኾን ሌሎች ባሕላዊ ክንዋኔዎችን የአርኪዎሎጂ ግኝቶችን እና ሌሎች ያልተደረሰባቸው ሃብቶችን መጠቀም እና ማስተዋወቅ ይገባል ነው ያሉት። በአርኪዎሎጂ ግኝቶች አዳዲስ ቅርሶች እየተገኙ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።

በአካባቢው ያለውን የማር ምርትም መጠቀም እንደሚገባም አመላክተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖች ድጋፍ ተደረገላቸው።
Next article“ልደቱ ልደታችን ነውና በመተሳሰብ እና በፍቅር እናሳልፈዋለን” ብጹዕ አቡነ አብርሐም