
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 28/2017 ዓ.ም(አሚኮ) ከ700 በላይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወገኖች ድጋፍ ማድረጉን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ አስታውቋል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ተወካይ እና የገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ኃይለማሪያም እሸቴ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎችን በመምረጥ የበዓል መዋያ ሥጦታ ተበርክቶላቸዋል ብለዋል።
ሰው ተኮር ተግባርን ለማከናወን አንዱ ማሳያ ምንም ገቢ የሌላቸው ወገኖችን በማሰብ የበዓል መዋያ ስጦታ ማበርከት ነው ያሉት አቶ ኃይለማሪያም ይህን መሰል የመደጋገፍ ሥራን ማከናወን እንደ ሀገር ያለንን ታላቅ እሴት የሚያመላክት እንደኾነ ገልጸዋል። አቶ ኃይለማሪያም በከተማዋ የሚገኙ ባለሃብቶች እና ወጣቶች ይህን የመደጋገፍ እና የመረዳዳት ባሕል አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ የሴቶች፣ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ምክንያት በማድረግ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ሴቶችን፣ ሕጻናትን፣ አካል ጉዳተኞችን እና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎችን ባማከለ መልኩ 714 ወገኖች ተለይተው ድጋፍ ተደርጎላቸዋል ብለዋል።
ድጋፉም 1ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ወጭ የኾነበት የፊኖ ዱቄት፣ የዶሮ እና የምግብ ዘይት መኾኑን ነው ወይዘሮ ሰብለ የተናገሩት። መምሪያ ኀላፊዋ በዓላትን ታሳቢ በማድረግ በክፍለ ከተሞች እና በመምሪያ ደረጃ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ በቀጣይ ቀናት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከዓይነት ድጋፍ እስከ ማዕድ ማጋራት እንደሚደረግም ጠቁመዋል።
ወይዘሮ ወርቄ ጋሻው የጣና ክፍለ ከተማ ነዋሪ እና የሦሥት ልጆች እናት ናቸው። በተደረገላቸው የዶሮ፣ ዘይት እና ፊኖ ዱቄት ድጋፍ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቷቸዋል። የፋሲሎ ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ አዝመራው ወርቁ” በተሰጠኝ ድጋፍ በዓልን ተደስቼ እንድውል ያስችለኛል ነው ያሉት። ሌሎችም ዝቅተኛ ነዋሪዎችን እንዲያስቡ ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!