
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በበዓሉ ወቅት የእሳት አደጋ እንዳይከሰት የኤሌክትሪክ ማብሰያዎች እና ከሚቀጣጠሉ ነገሮች ላይ ጥንቃቄ እንዲደረግ የባሕር ዳር ከተማ እሳት እና ድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ጥሪ አቅርቧል፡፡ የባሕር ዳር ከተማ እሳት እና ድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ቡድን መሪ ሁሴን እንድሪስ ኅብረተሰቡ በዓሉን ሲያከብር ከእሳት እና ድንገተኛ አደጋ አጋላጭ ከኾኑ ነገሮች ራሱን መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በተለይም ምግብ በማብሰል ወቅት የኤሌክትሪክ ጫና ስለሚፈጠር እና ድንገተኛ አደጋ ሊከሰት ስለሚችል የሶኬት አጠቃቀም ላይ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ከሰል፣ ሻማ፣ ሲሊንደር እና ሌሎች ተቀጣጣይ ነገሮችንም በጥንቃቄ መጠቀም መኖር እንዳለበትም መክረዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ እሳት አደጋና ድንገተኛ አገልግሎት የልደት በዓል በሚከበርበት ወቅት የእሳት እና ድንገተኛ አደጋዎች እንዳይደርሱ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
ለበዓሉ አራት ከባድ ተሽከርካሪ መኪኖች፣ በሦስት ፈረቃ የሚሠሩ ሠራተኞችን እና ሌሎች አደጋን ለመከላከል ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ ቁሳቁሶችን በማዘጋጀት የ24 ሰዓት አገልግሎት ለመስጠት የቅድመ ዝግጅት ሥራውን ማጠናቀቁን ቡድን መሪው ገልጸዋል፡፡
አደጋዎች ሲያጋጥሙ በስልክ ቁጥር 058 220 00 22 ወይም 058 320 26 30 በመደወል አገልግሎት ማግኘት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!