
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሕግን ተላለፉ፣ አንድያ አጋዣቸውን በደሉ፣ ኀይልም ከእነሱ ራቀ፣ ክብርም ከእነሱ ላይ ተነሳ፣ እራቁታቸውን እንደኾኑም አወቁ፣ ይህን ያወቁት ግን ዘግይተው ነበር፣ የሠሩት ጥፋት ሀፍረትን እንዳከናነባቸው ባወቁ ጊዜ ተደበቁ። እንደጠፉ ከመቅረት ይልቅ ግን መዘግየት ይሻላልና ከልብ ተጸጸቱ ረዳታቸው የዓለምን ፈጣሪ ከልባቸው አቅንተው ጠየቁ። ለ40 ቀናትም ሱባኤ ገቡ።
ይሁን እንጅ የጥንቱ ጠላታቸው አርፎ ሊተኛ ግን አልቻለም። ከገቡት የመጸጸት ጉዞ ሊያሰናክላቸው ብዙ ጣረ። በመጨረሻም አሁንም ባቀረበው ማታለያ ተታለው ሱባኤያቸውን ሊያገባድዱ ትንሽ ሲቀራቸው አሁንም ተሳሳቱ ፈጣሪያቸውንም አሳዘኑ። ይሄኔ ምርር ብለው አለቀሱ፤ ፈጣሪያቸው የጠላታቸውን ምክር ያውቃል፤ ሳይፈልጉ ከመስመራቸው እያወጣቸው፤ ሕግ እንዲተላለፉ እያደረጋቸው እንደኾነም ያውቃል። ይህን ምክር እና ደባ ለመሻር እና ለማንኮታኮት ፍቅር እና ሰላም ወሳኝ እንደኾነ አውቆ ራሱን ዝቅ አደረገ።
ከልጅ ልጃቸው ተወልዶ ፍቅር እና ይቅርታን በተግባር ኑሮ ሊያሳያቸው የዕዳ ደብዳቤአቸውንም ሊቀድላቸው ቃል ገባላቸው። የባሕር ዳር ደብረ ሲና ባዕታለማርያም ገዳም የስብከተ ወንጌል ክፍል ኀላፊ መምህር አብርሃም ሞላ የበዓላት ሁሉ ራስ የኾነው የልደት በዓል ለሰው ልጅ ልዩ በዓል ነው ብለዋል።
ኢየሱስ ስለምን ተወለደ ቢሉ የሰውን ልጅ ለማዳን ተወለደ፤ የጠፋውን የሰው ልጅ ሊፈልግ ተወለደ፤ በሞት ጥላ ስር ያለውን የሰው ልጅ ለማዳን፣ በሱራፌል ሰይፍ የተዘጋውን ገነት ሊከፍት፣ በፍጡር ሊሟሉ የማይችሉትን ለመሙላት በስጋ ተገለጠ ብለዋል። የሞት ደብዳቤን ፍቆ የሕይዎት ደብዳቤ ለሰው ልጆች ሊሰጥ ተወለደ ነው ያሉት።
የዓለም ፈጣሪ ለአዳም የገባውን ቃልኪዳን ሊፈጽም መወለዱንም ተናግረዋል። ከሰዓቱ አንድ ሰዓት፣ ከዕለቱ አንድ ዕለት፣ ከወሩ አንድ ወር ከዓመቱ አንድ ዓመት ሳያፈርስ ሳይቀንስ ሳይጨምር ተወልዶ ዓለምን ስለማዳኑ አብራርተዋል። አዳም በሠራው የሕግ መተላለፍ ምክንያት ከገነት ከተባረረ በኋላ አምላኩ 5 ሺህ 500 ዘመን ሲኾን ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ ባለው ቃል ኪዳን መሠረት ሳይጨምር ሳይቀንስ እንደፈጸመለትም ነግረውናል።
ፈጣሪ ወደ ምድር ለምን መጣ ከተባለ ችግረኞችን ሊረዳ፣ የደከሙትን ሊያበረታ እና ያለ ልዩነት ዓለምን ሊያድን እንደመጣ አስገንዝበዋል። አዳም ከበደለ በኋላ ከፍጥረታት ጋር መጣላቱን የነገሩን መምህሩ ክርስቶስ ሲወለድ ጠላት ኾነውበት የነበሩት ፍጥረታት እንደታረቁት እና ታዛዥ እንደኾኑለት አብራርተዋል።
ክርስቶስ ቆሽሾ የነበረውን የሰውን ልጅ ባሕሪ ለማክበር መወለዱን ተናግረዋል። ክርስቶስ የሰውን ልጅ ዳግም ይፈጥረው ዘንድ ስለመወለዱም አብራርተዋል። ክርስቶስ የተወለደው ዲያብሎስ በሰው ልጅ ላይ የመከረውን ሥራ ሊያፈርስ ተወልዷል፤ የሰው ልጅ በሰይጣን የተቀማውን ደስታ ለመመለስ ተወልዷል፤ ክርስቶስ ሲወለድ የራቁ ቀርበዋል፤ ያዘኑት ተጽናንተዋል፤ የተከዙት ተደስተዋል፤ የተራቡት ጠግበዋል፤ የተጠሙትም ጠጥተዋል ሲሉ ይናገራሉ።
በልደቱ ሰባት ነገሮች ታርቀዋል የሚሉት መምህሩ በክርስቶስ መወለድ ሰው እና እግዚአብሔር ታርቀዋል፤ ነፍስ እና ስጋ፣ ሰው እና መላዕክትም በመካከላቸው የነበረውን ጥል አፍርሶታል ብለዋል። ክርስቶስ ሲወለድ ጥላቻ ፈርሷል የሚሉት መምህሩ አሁን ላይ በሀገሪቱ የሚታየው ጥላቻ እና መራራቅ፣ ደም መፋሰስ ይቆም ዘንድ ሰዎች ከክርስቶስ መማር እና ሰላምን ማውረድ ይገባቸዋል ነው ያሉት።
ሰዎች የሰላም ካባ እና መጎናጸፊያ ሊጎናጸፉ እንደሚያስፈልግም ነግረውናል። የፍቅር ዘውድ የደፋ ሰው የክርስቶስን መወለድ በትክክል እንደሚያከብር አስገንዝበዋል። መምህሩ ከዚህ ውጭ በኾነ መንገድ በጥላቻ ከኾነ ፈጣሪ በረከትን እንደማይሰጥ ጠቁመዋል። ወንድም ወንድሙን ሊያከብረው፣ ሊቀርበው እና ሊወደው እንደሚገባም ገልጸዋል።
በልደት በዓል ይቅር መባባል እና ስለሰላም ከልብ መሥራት እና ሰላምን አጥብቆ መያዝ እንደሚያስፈልግም ነው የተናገሩት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!