
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በአብዛኛው የዓለም ሀገራት ዘንድ በጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ታኅሣሥ 25 የሚከበር በዓል ነው። በሀገራችን ደግሞ የልደት በዓል በየዓመቱ ታኅሣሥ 29 ቀን የሚከበር ደማቅ በዓል ነው። ከአራት አመት አንድ ጊዜ ወይም በዘመነ ዮሐንስ ደግሞ ታኅሣሥ 28 ቀን ይከበራል። ይህ በዓል በተለይ በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ደማቅ ትርጉም ያለው ነው።
የዚህ ዓመት የልደት በዓል ግብይት በባሕር ዳር ከተማ ሞቅ ደመቅ ብሎ ተስተውሏል። በዓሉ ሲነሳ አብረው የሚመጡ ግብዓቶችም በብዛት ሲገቡ ታይተዋል። በሬ እና ፍየሉ፣ ዶሮው እና በጉ፣ ሌላውም ለበዓል ገበታ የሚቀርብ ሁሉ በየገበያው ደርቷል። የሻጩ እና ሸማቹ የገበያ ላይ ትርምስ ልዩ ድባብ ፈጥሯል። ሰዎች በዓሉን ቤት ባፈራው እና አቅም በፈቀደ ለማሳለፍ ከላይ ታች ሲሉ ማየት ልዩ ድባብ አለው።
እኔም ታድያ ሞቅ ደመቅ ባለው እና በደራው ገበያ ላይ ተገኝቼ የግብይት ቅኝት አድርጊያለሁ። የመጀመሪያ መዳረሻችን ደግሞ የከብት ተራ ነው። ቅኝት ያደረግንበት በተለምዶ አጠራሩ ካንፕ የበሬ፣ የፍየል እና የበግ ተራ ከዳር እስከ ዳር ሞልቷል። በዚህ የገበያ ማዕከል ላይ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ የዋጋ ተመን ድረስ የሚጠሩ የዕርድ እንስሳት ቀርበዋል። በሬ በጥሪ ደረጃ ከ35 ሺህ እስከ 110 ሺህ ድረስ ይጠራል። አንድ የደለበ ኮርማም በ92 ሺህ ብር ሲገበያዩ ተመልክቻለሁ።
በዚሁ ገበያ የበግ እና ፍየል ግብይትም ደርቶ ውሏል። የበግ ግብይት በጥሪ ደረጃ ከአምስት ሺህ እስከ 17 ሺህ ብር ድረስ ይጠራል። ትልቅ የሚባል የፍየል ሙክት ደግሞ እስከ 18 ሺህ ድረስ ዋጋ ተቆርጦለታል። ወጣት ንብረት ሞላ ከሻውራ-ባሕር ዳር የፍየል ነጋዴ ነው። የፍየል ንግዱ ካምናው ተመሣሣይ ወቅት አንጻር የበዛ ልዩነት የለውም ሲል ገልጿል።
ከጓደኞቻቸው ጋር በሬ ለመግዛት እየተከራከሩ ያገኘኋቸው እና ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አባት ሌላው ስለግብይቱ ሀሳብ የሰጡኝ ነበሩ። የኮርማ በሬ ዋጋ ካምናው አንጻር ያልተጋነነ ቢኾንም ጭማሪ አለው ብለውኛል። የእርድ እንስሳቱ በየአይነቱ መግባቱ ግን መልካም ነው ብለውታል። ሌላው የዶሮ እና የእንቁላል ገበያ ግር ግሩ እና ሽር ጉዱ ገራሚ ነው። የበዓል ገበያው፣ የሸማቹ እና ሻጩ ኹካታ ልዩ መልክ አለው። አንዳች ደስ የሚል ነገር አለው። የሰው ግፊያ አይሰለችም። ልዩ ቀለም የኾነች ሀገር እንዳለችን ማሳያ ነው።
በዚህ የበዓል ግርግር የዶሮ ዋጋ በደረጃ ነው። ከ5 መቶ እስከ 9 መቶ 50 ብር ድረስ ሲገበያዩ አስተውያለሁ። እንቁላልል ከ11 ብር እስከ 13 ብር ድርስ ይሸጣል። ቀይ ሽንኩርት ከ85 እስከ 100 ብር ድረስ ሲጠራም ነበር። ብቻ የልደት በዓል በባሕር ዳር ከተማ የደራ ነበር ብዬ የራሴን ፍርድ ሰጥቼ፣ ግርግሩን የገበያ ቅኝት አጠናቅቄ ተመለስኩ። ባሕላችን እና ወጋችን ውብ ቀለም መኾኑንም በቅኝቴ ታዘብሁ።
የልደት በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ፈጣሪ የሰውን ልጅ ለማዳን አንድ ልጁን በቤዛነት የሰጠበትን እና አምላክ ሰው የኾነበትን ምሥጢር ታሳቢ በማድረግ የሚከበር በዓል ነው። የከርሞ ሰው ይበለን። ሰላም!
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!