
ሰቆጣ: ታኅሣሥ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያሥተላለፉት የዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ በርናባስ ሰላም እና ትህትና ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የተገኙ ገጸ በረከቶች ናቸው ብለዋል።
በታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጅ ፍቅር ወልድን ከልዕልና መንበሩ ስቦ እስከሞት ድረስ አደረሰው በማለት በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ዕውነተኛ ሰላም መገኘቱን ብጹዕነታቸው ተናግረዋል። የሰው ልጆችም ከገባንበት መለያየት እና መገዳደል ወጥተን በዓሉን ማክበር ብቻ ሳይኾን ዘላቂ ሰላም እንዲኖር በጋራ ልንሠራ ይገባል ሲሉ አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል።
በሀገር ውጭም ኾነ በሀገር ውስጥ ለሚኖሩ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮችም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። የዘንድሮው የልደት በዓል ለየት የሚያደርገው በአማራ ክልል ብሎም በዋግ ኽምራ አንጻራዊ ሰላም በተገኘበት ነው ያሉት የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ዋና አሥተዳዳሪ ኃይሉ ግርማይ ናቸው።
ለተገኘው ሰላምም የጸጥታ መዋቅሩ ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር በመኾን የከፈሉት መስዋዕትነት ከፍተኛ መኾኑን ተናግረዋል። አሥተዳዳሪው ከእጃችን ያለውን ሰላም አጽንቶ ለማስቀጠል የአማራ ክልል ሕዝብ ብሎም የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ማኅበረሰብ እንደተለመደው ከጸጥታ መዋቅሩ እና ከሰላም ጎን ሊቆሙ ይገባል ነው ያሉት።
በማወቅም ኾነ ባለማወቅ ወደ ጫካ የገቡ የታጠቁ ኀይሎች መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ከሕዝባቸው እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር በዓሉን እንዲያከብሩም አቶ ኃይሉ ጥሪ አቅርበዋል። ተካፍሎ መብላት ባሕሉ የኾነው የዋግ ሕዝብ ብሎም የክልሉ ሕዝብ የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ልደትን አስቦ እንዲውልም አሳስበዋል።
ዋና አሥተዳዳሪው በተለይም በዋግ ኽምራ ደጋማ ወረዳዎች ባለፈው ክረምት በተከሰተው ከፍተኛ የዝናብ መጠን ምክንያት በተፈጥሮ አደጋ የተጎዱ የዳህና፣ የጋዝጊብላ እና የጻግቭጂ ወረዳ ማኅበረሰብን ሁሉም እንዲረዳ እና ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል። በዓሉ ለመላው የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ኢትዮጵያውያን የሰላም፣ የፍቅር እና የብልጽግ እንዲኾን መልካም ምኞታቸውንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!