
አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ወገኖች የልደት በዓል መግደፊያ ድጋፍ አደርጓል። ወይዘሮ ሽዋዬ በቀለ በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ናቸው። ከራሳቸው ጋር ስምንት ቤተሰብ እንደሚያስተዳድሩ የነገሩን ወይዘዋ የልደት በዓልን ለመግደፍ እና እንደሌሎች ተደስተው ለመዋል አቅም እንደሌላቸው አንስተዋል።
ይሁን እንጅ ዛሬ በከተማ አሥተዳደሩ በኩል 5 ሊትር ዘይት፣ 20 ኪሎ ፊኖ ዱቄት እና አንድ ዶሮ እና እንቁላል እንደተበረከተላቸው ነው የገለጹት። የተደረገላቸው ድጋፍም በዓልን እንደ ሌሎች ነዋሪዎች በደስታ ለማሳለፍ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል። እንደ ወይዘሮ ሽዋዬ ሁሉ በከተማ አሥተዳደሩ በዝቅተኛ ኢኮኖሚ የሚተዳደሩት ሌሎች ነዋሪዎችም የልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
ድጋፉን ላበረከቱላቸው ተቋማት እና በጎ አድራጊ ግለሰቦችም ምሥጋና አቅርበዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ከ4ዐዐ ሺህ በላይ ለሚኾኑ ወገኖች የበዓል መግደፊያ ድጋፍ ማድረጉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል።
የተደረገው ድጋፍ የዘይት፣ ፊኖ ዱቄት፣ ዶሮ እና እንቁላል ነው። ድጋፉ ከተቋማት፣ ከከተማው በጎ አድራጊ ግለሰቦች መገኘቱን ከንቲባዋ ጠቅሰዋል። ድጋፉን ላበረከቱ ተቋማት እና በጎ አድራጊ ግለሰቦች ምሥጋና አቅርበዋል። በከተማው ድጋፍ የሚሹ በርካታ ወገኖች እንዳሉ የገለጹት ከንቲባ አዳነች አበቤ ኅብረተሰቡ የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ እና በመደገፍ በዓሉን እንዲያሳልፍም ጠይቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!