የእርድ ሥርዓቱ ጤናማ እንዲኾን ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል።

19

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኀይሉ ዓለሙ በከተማ አሥተዳደሩ ለልደት በዓል በማኅበር የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች የእርድ እንስሳትን እያቀረቡ ይገኛሉ ብለዋል። እስከ አሁንም 241 ሺህ 257 የሥጋ ደሮዎችን፣ ከ360 ሺህ በላይ የደለቡ በጎችን እና ፍየሎችን፣ ከ140 ሺህ በላይ ሰንጋዎችን ማቅረብ እንደተቻለ ነው የተናገሩት።

ከጎንደር ከተማ ባለፈ ለመተማ፣ ሁመራ፣ አፋር እና ሌሎች አካባቢዎች ጭምር እያቀረቡ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ከ150 ቶን በላይ ወተትም ተዘጋጅቶል ነው ያሉት። በከተማው በሚገኘው የወተት ፋብሪካ በቀን እስከ 10 ሺህ ሊትር ወተት በማቀነባበር ቅቤ፣ አይብ፣ እርጎ እና የታሸገ ወተት ለማኅበረሰቡ እየቀረበ ነው ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ በመደበኛ ሥራ ላይ የተሠማሩ አድላቢዎች እና አርቢዎች የተለያዩ እንስሳትን እና የእንስሳት ተዋጽኦዎችን እያቀረቡ መኾኑን ነው ያነሱት። በከተማ አሥተዳደሩ የእርድ እንስሳትን ከማቅረብ ባለፈ “የእርድ ሥርዓቱም ጤናማ እንዲኾን ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል” ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ በዓለም ባንክ እየተገነባ የሚገኘው ቄራ እስኪጠናቀቅ በጊዜያዊነት ምርመራ የሚያደርጉ በእንስሳት ባለሙያዎች የታገዙ ኢንተርፕራዞች ተደራጅተዋል ብለዋል። ማኅበረሰቡ የእርድ እንስሳትን በኢንተርፕራይዞች አስመርምሮ እርድ እንዲፈጸም ይደረጋል ነው ያሉት።

ሥጋ ቤቶችም ጥራት ያለው ሥጋ ለማኅበረሰቡ እንዲያቀርቡ የግንዛቤ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በጥንታዊ ሥልጣኔ የደመቀች፤ በአኩሪ ታሪክ የታወቀች፤ በመንፈሳዊ ጥበብ የመጠቀች”
Next article“እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)