
ወልድያ: ታኅሣሥ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ብዙዎች የትናንታቸውን ጥለዋል፤ ታሪክ እና ትዝታቸውን አጥተዋል፤ ወግ እና ባሕላቸውን ተነጥቀዋል። የትናንት የሚሉት ማንነት፣ በትዝታ የሚያመጡት ዕውነት፣ በመዝገብ የሚይዙት እኔነት፣ ለልጅ ልጅ የሚነግሩት የታሪክ ሰንሰለት የላቸውም። ነጻነታቸውን አጥተዋል።
ሉዓላዊነታቸውን ተነጥቀዋል። በቀኝ ገዢዎቻቸው ቀንበር ሥር ገብተዋል። የገዢዎቻውን ባሕል እና ሃይማኖት ተቀብለዋልና የሚመኩበት፣ የሚተርኩት፣ የሚያስተምሩት የታሪክ ሰንሰለት የላቸውም። ይልቅስ የቀኝ ገዢዎቻቸውን ቋንቋ ይናገራሉ። በቀኝ ገዢዎቻቸው ባሕል ይኖራሉ። በቀኝ ገዢዎቻቸው ወግ እና ሥርዓት ይመላለሳሉ እንጂ።
ከሁሉም የተለየች፣ ነጻነቷን ያጸናች፣ ሉዓላዊነቷን ያስከበረች፣ የትናንቱን የጠበቀች፣ አጽንታ ያኖረች፣ ዜማን ከእነ ምልክቱ፣ ሃይማኖትን ከነሥርዓቱ እና ከነትውፊቱ ያቆየች፣ ታሪኳን በራሷ ቋንቋ ሲሻት በአለት ላይ፣ ስትፈልግ በብራና እንዲያም ሲል በወረቀት የጻፈች፣ ከጥንት እስከዛሬ ያለ ታሪኳን ሳታቋርጥ ለልጅ ልጅ የተረከች፣ ነጻነት እና ድል አድራጊነትን ለትውልድ ሁሉ ያወረሰች ድንቅ ሀገር አለች።
ከሰማየ ሰማያት ዜማን የቀዳች፣ የተውሶ ባሕል እና ትውፊት ያልተቀበለች፣ የራሷንም ያልጣለች፣ ዓለምን ሁሉ በጥበብ ሥራዎቿ ያስደነቀች፣ ለዓለምም በረከት የኾነች፣ ምድርንም በጥበብ ያስጌጠች እንቁ አለች። እጹብ የሚያሰኝ ሃይማኖታዊ ሥርዓት የሚፈጸምባት፣ ያለ ማቋረጥ ጸሎት የሚደርስባት፣ የአምላክ ስም እየተጠራ ምሥጋና የሚቀርብባት፣ አምላክ በረከቱን የማይነሳት፣ አብዝቶ የወደዳት፣ ጎዳናዎቿን የባረከላት፣ ዋሻዎቿን እና ሐይቆቿን የቀደሰላት የጥበብ ማሕተም ናት ኢትዮጵያ።
ኢትዮጵያ በጥንታዊ ሥልጣኔ የደመቀች፤ በአኩሪ ታሪክ የታወቀች፤ በመንፈሳዊ ጥበብ የመጠቀች፤ በትውፊት የጠለቀች ናት። እርሷ በባሕሏም፣ በታሪኳም፣ በሃይማኖቷም ድንቅ ናት፤ ድንቅ ምስጢርም አላት። አበው ከሁሉ የሚያልቃትን ሠርተውላታል፤ መልካም እመቤት አድርገው አኖረዋታል፤ ከሁሉ ልቃ ኖራለች። ለማንም ሳትገብር እና ሳትበገር ትከብራለች እና ከሁሉ የላቀ ሃይማኖታዊ ሥርዓትን ታከብራለች።
እንደርሷ አድርገው በዓላትን በሥርዓት የሚያከብሩ፣ ሃይማኖትን የሚጠብቁ የሉም። ለዛም ነው እርሷ ሃይማኖታዊ በዓላትን በምታከብርበት ጊዜ ብዙዎች አይለፈን እያሉ ከሩቅ እየገሰገሱ በደጇ የሚሠባሠቡት። የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በኢትዮጵያ በድንቅ ሥርዓት ይከበራል። ይሄም ከሁሉም የተለየ ያደርገዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ግን ዓለምን እጹብ የሚያሰኘውን ሥርዓት ታከብራለች።
የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል እና የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባቶች ከሌላው ዓለም ክፍል ካሉ የሃይማኖት ቤተሰቦቻችን የተሻለ ጥንካሬ እንደነበራቸው ቅዱሳን መጻሕፍት ያስረዱናል ይላሉ።
ገድላቱ፣ ድርሳናቱ መንፈሳዊነታቸውን፣ ጥንካሬያቸውን፣ ሥርዓት ጠባቂነታቸውን፣ እግዚአብሔርን የሚፈሩ መኾናቸውን ይገልጻሉና።
በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ አብዝተው እግዚአብሔርን የሚሹ ናቸው። ይህም ኢትዮጵያ በቀኝ ግዛት እንዳትያዝ የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል። በቀኝ ገዢዎች እጅ ሥር ባለመውደቋ ባሕላችን፣ ታሪካችን፣ ወጋችን፣ ሥርዓታችን ተጠብቆ ኖረ። በዚህም ምክንያት ሃይማኖታዊ ሥርዓታችን እና አከባበራችንም እንደተጠበቀ ነው ይላሉ ብፁዕነታቸው።
በቀኝ ግዛት ሥር የወደቁ ሀገራት ሃይማኖትም፣ ባሕልም፣ ታሪክም፣ ወግም ኖሯቸው ለልጅ ልጅ ማስተላለፍ አልተቻላቸውም። የእኛ የኢትዮጵያውያን የበዓል አከባበር ከሌሎች ደምቆ የሚታየው ግን ከአባቶቻችን የቆዬው ትውፊታችን ባለመቋረጡ ነው።
የቅዱስ ያሬድ የዜማ ስልቶች በየበዓላቱ ይፈጸማሉና ከሌሎቹ የክርስትና ዓለማት በተለየ መልኩ በዓላችን ደምቆ ይከበራል ነው የሚሉት።
በመንፈስ ቅዱስ የምትመራው፣ የትናንቱን ጠብቃ የምትኖረው፣ ሃይማኖትን ከነሥርዓቱ እና ትውፊቱ የምታከብረው ቤተክርስቲያን በገዳማቷ እና በአድባራቷ የመሠረቷትን፣ የጉልላቷን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት ከፍ ባለ ሥርዓት ታከብራለች።
ምሥጋና እና ውዳሴ ታቀርባለች። ሊቃውንቶቿ ከማዕልት እስከ ሌሊት በጽናት ቆመው በዝማሬ ይተጋሉ። በውዳሴ ይበረታሉ።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!