የልደት በዓል የተጣሉ ፍጥረታት የታረቁበት ዕለት ነው።

25

ፍኖተ ሰላም: ታኅሣሥ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ከሚከበሩ በዓላት መካከል የኢየሱስ ክርሰቶስ የልደት በዓል አንዱ ነው። በዓሉ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ክዋኔዎችን አቅፎ የያዘ ነው። በተለይም በበዓሉ ዕለት የገና ጨዋታ በብዛት ይከወናል። ይህ በዓል ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ የክዋኔ ይዘቱን ሳይለቅ ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፍ ዘንድ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ገልጿል።

”ገናን በፍኖተ ሰላም” በሚል መሪ መልዕክት ለአራተኛ ጊዜ የገና ጨዋታ በዓል አከባበር መርሐ ግብር በፍኖተ ሰላም ከተማ ተካሂዷል። የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ተወካይ ኀላፊ ዘውዱ ደግ አረገ የገና ባሕላዊ ጨዋታን እና ሃይማኖታዊ አስተምህሮውን ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ በማድረግ አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ዓላማ ያነገበ መኾኑን ገልጸዋል።

የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ማማሩ ሽመልስ በተለያዩ ጊዜያት በሚያጋጥሙ ችግሮች የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት የገና ጨዋታ እንደ ከተማ ባሕላዊ ጨዋታ ኾኖ በየዓመቱ እንዲከበር በርካታ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። የምዕራብ ጎጃም ዞን ሀገረ ስብከት ሥራ አሥኪያጅ መጋቢ ሃይማኖት ኪነ ጥበብ ገብረ ኢየሱስ የልደት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን መወለዱን የምንማርበት፤ የተጣሉ ፍጥረታት የታረቁበት ዕለት መኾኑን ገልጸዋል።

ሥራ አሥኪያጁ አማኞች በዓሉን ሲያከብሩ በደስታ፣ በፍቅር እና በመቻቻል መኾን እንደሚገባውም ተናግረዋል። ይህ በዓል በድምቀት እንዲከበር እና የአደባባይ በዓል እንዲኾን የምዕራብ ጎጃም ዞን ሀገረ ስብከት ከከተማ አሥተዳደሩ ጋር በመኾን እንደሚሠራ ነው የገለጹት። በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የምዕራብ ጎጃም ዞን ሰላም እና ፀጥታ መምሪያ ኀላፊ ሙሉጌታ አለም የገና ባሕላዊ ጨዋታን በድምቀት ለማክበር አኹን የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም ወደ ተሟላ ሰላም ማሸጋገር ይገባል ብለዋል።

ሰላምን ለማስፈን ሁሉም ሊረባረብ ይገባልም ነው ያሉት። በመርሐ ግብሩ ላይም የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን የተመለከቱ መንፈሳዊ ዝማሬዎች፣ ተውኔት እና የገና ባሕላዊ ጨዋታ በወጣቶች ቀርበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በማረፋቸው የተሰማኝን ሃዘን እገልጻለሁ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next article“በጥንታዊ ሥልጣኔ የደመቀች፤ በአኩሪ ታሪክ የታወቀች፤ በመንፈሳዊ ጥበብ የመጠቀች”