ወደ ልመና የወጣው አባት?

32

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ባለሁበት ባሕርዳር ከተማ በአንዱ ቀበሌ ያገኘዋቸው የከባድ ጭነት መኪና አሽከርካሪ የባሕርዳር ነዋሪ እንደኾኑ እና ሦስት ልጆች እንዳሏቸውም አጫወቱኝ፡፡
ሰውየው አሁን ላይ ተስፋ ያለው ነገር እየታያቸው እንደኾነ ቢናገሩም ገና ዋናው ሥራቸውን ግን አልጀመሩም፡፡ ለሥራቸው ማቆም ምክንያት የኾናቸው ደግሞ በሀገር ደረጃ የተከሰተው ግጭት እና አለመረጋጋት እንደኾነ ይናገራሉ፡፡
በሥራቸው ጥሩ የሚባል ገቢ የሚያገኙ፣ ልጆቻቸውን ከግል ትምህርት ቤት ያስተምሩ የነበረ እና በኑሯቸው ደስተኛ እንደነበሩ ነው የነገሩን፡፡
ነግር ግን ግጭቱን ተከትሎ የተሽከርካሪው ባለቤት ለንብረቱ በመስጋት መኪናው እንዲቆም በማድረጉ ከሥራ ተለያዩ።

አሽከርካሪው በኑሮ መፈተን የጀመርኩት ሥራ ባቆምኩበት ማግስት ነው ይላሉ፤ ሌሎች ተሽከርካሪዎችን በማፈላለግ ለመቀጠር ቢሞክሩም ማግኘት ግን አልቻሉም፡፡
ለጥቂት ወራቶች ያጠራቀሟትን የተጠቀሙት አሽከርካሪው የቤት ኪራይ መክፈል፣ ለልጆቻቸው የትምህርት ቤት ክፍያ ማጣትን ጨምሮ ብዙ ፈተና ገጥሟቸዋል።

አንድ ቀን እሑድ እኔ እና ባለቤቴ ልጆቻችን ይዘን ቤተክርስቲያን ሄድን፤ ስንመለስ የሚበላ የለም ኪሴን ዳበስኩ አስር ብር ብቻ አለችኝ በዛች አስር ብር ለልጆቹ ብስኩት በመግዛት ሰጠኋቸውና ሲበሉ አየሁ ብስኩቷ እንዳላጠገበቻቸው ሳይ በጣም አዘንኩ እንባየ ተናነቀኝ ይላሉ፡፡
ትልቁን ልጀን ይዠ እኖርበት ከነበረው አካባቢ እርቄ ሄድኩ የሚሉት አሸከርካሪው ሰው ሊተላለፍበት የሚችል ቦታ ላይ ልጀን ቁጭ አደረኩና ፌስታል ዘርግቸ መለመን ጀመርኩ።
ልጀ አይን አይኔን ያየኛል ግራ ተጋብቷል፤ ሰዎች አለባበሳችንን አይተው እየተገረሙ ብር እየጣሉልን ማለፍ ጀመሩ ሲሉ ያሳለፉትን ኹኔታ ይገልጻሉ፡፡

በተጣለልኝ ገንዘብ ለባለቤቴ እና ለልጆቸ ምን አይነት ምግብ ገዝቸ እንደምገባ እያንሰላሰልኩ እያለ ስሜ ሲጠራ ሰማሁ የሚሉት አሸከርካሪው ቀና ስል ከተከራየሁበት አካባቢ የሚኖር ጎረቤቴ ነው። በጣም አፈርኩ የሚሉት አሸከርካሪው ምነው ሲለኝ እንባየን መቆጣጠር አልቻልኩም። ጓደኛየ ደነገጠ መጣና አቀፈኝ ምንድን ነው የተፈጠረው ብሎ ጠየቀኝ ያሳለፍኩትን እና እያሳለፍኩት ያለውን ፈተና በእንባየ ታጅቤ ገለጽኩለት።

ጎረቤቴ በጣም አዘነ አይኑ እንባ አቅርሯል፤ የዘረጋሁትን ላስቲክ እስከ ብሩ ሽክፍ አድርጎ አነሳው በልና ተነስ እንሂድ አለኝ፤ ቆይ ትንሽ ልለምን አልኩት በፍጹም አንተ አትለምንም፤ እንሂድ ብሎ ወደ ሰፈር እኔ እና ልጀን ይዞን ሄደ ሰፈር ስንደርስ የአካባቢው ሰው የሚበላ ሰጡን። የታየኝ የሰጡኝን ይዠ ከቤት ላሉት ልጆቸ እና ለባለቤቴ መውሰድ ነበር በማለት አስታወሱ።

“የሰጡኝን ምግብ ለልጆቸ እና ለባለቤቴ ሰጠኋቸው፤ ልጆቻችን በልተው የሚጠግቡ አልመስለንም፤ የልጆቻችን መጥገብ ስናይ እኛ መብላት ጀመርን። ባለቤቴን ትኩር ብየ አየኋት ቆንጆ ናት።
ግን በፊት በምቾት ተይዛ ከፊቷ የሚቀዳው ወዘና የለም፤ አሁን ነው ያስተዋልኳት ጠቆር ቆር ብላለች።

ዛሬስ እንዲህ በላን ቀጣይ ምን ማድረግ ነው ያለብኝ ምንድን ነው የምሠራው ብየ ከራሴ ጋር መታገል ጀመርኩ” እንዴት ነው ትዳሬን ምመራው? ልጆቸንስ እንዴት ነው የማሳድጋቸው? ይህ አኗኗር እስከመቸ ነው የሚቀጥል? ግራ ግብት ብሎኛል” በማለት ከዛሬ በላይ ነገ እንዳስፈራቸው አወጡ አወረዱ።
“በዚህ መሀል አንድ ቀን በር ተቆረቆረ እና እንዴት ዋላችሁ ብለው መንገድ ላይ ያገኘኝ ጎረቤቴ እና አንድ ሰው ወደ ውስጥ ገብተው ቁጭ አሉ።
ተከታትለው ሌሎች ሴቶች ጎረቤቶቻችን ወደ ውስጥ ገብተው በማዳበሪያ የጤፍ ዱቄት፣ እንጀራ በትሪ ይዘው መጥተዋል፤ እኔ ሁሉም ነገር ህልም ነው የመሰለኝ አሉን።

ባለቤቴም ባየችው ነገር ተደናግጣ ጥግ ይዛ ቆማ የሚኾነውን ታያለች፤ መጀመሪያ ያገኘኝ ጎረቤቴ እኛ እያለን አንተ በዚህ ኹኔታ አትቀጥልም፤ ለጊዜው ይህ ከሰፈር ሰዎች የተሠበሠበ ነው ብሎ የተጠቀለለ ብር ሰጠኝ፤ ሁለተኛው ሰው ልጆችም ትምህርት ቤት እንዳቋረጡ ሰምተናል ነገ ጀምሮ ትምህር ቤት እንዲጀምሩ አድርግ እስኪመቻች ድረስ ክፍያውን እኛ እንሸፍናለን አሉኝ፤ ይህ ጊዜ ያልፋል ዋናው እኛ ደህና እንሁን ሁሉም ነገር ይስተካከላል አይዞህ አሉኝ” ብለውናል፡፡

ምንም ቃል ሳላወጣ እንባየ ይወርዳል፣ ባለቤቴም ታለቅሳለች። ልጆቸ አንጋጠው እኛን ያያሉ በቃ አሁን እኮ ሁሉም ነገር ተስተካከለ በቃ አለ መጀመሪያ ያገኘኝ ጎረቤቴ ሲሉ በትዝታ ውስጥ ኾነው ነው። ጎረቤት ማለት እኮ በደስታ ጊዜ ሲኖርህ ብቻ እየተጠራራህ፣ እየደገስክ በፌሽታ እና በደስታ ማሳለፍ ብቻ አይደለም። እንዲህም ችግር ሲኖር ተነጋግረን ችግሩን ተጋርተን ማለፍ መቻል ነው ያለብን እኛን ሳታማክር ለመለመን መወሰንህ ትክክል አይደለም በጣም አጥፍተሀል ብለው ወቀሱኝ ነው ያሉት፡፡

እኔም ልክ መኾናቸውን ተናግሬ ይቅርታ ጠየቅሁ የሚሉት አሸከርካሪው ለልጆቸ ብስኩት ገዝቸ ሲበሉ ሳይ የተሰማኝ ስሜት ጠፍቶ ፍልቅልቅ ፊታቸውን እያየሁ ከጎረቤቶቸ ጋር እየተጨዋወትን የተፈላውን ቡና መጠጣት ጀመርን፤ ቡናው እንዳበቃ ከዚህ በኋላ ይቸግረኛል ብለህ እንዳታስብ ሁሉም ነገር መስመር ይይዛል ብለው ተሰናብተውን ወጡ፤ እኔም ምሥጋናየ ያደረጉልኝን እንደማይመጥን ባውቅም ምሥጋናየን አዥጎድጉጀ ሸኘኋቸው ብለዋል፡፡
ዛሬ ይህን ያደረገ አምላክ ነገን እንደማይተወኝ በማመን ከባለቤቴ እና ከልጆቸ ጋር ደስ ብሎን ስንጫዎት አሳለፍን፡፡

አንድ ቀን ታዲያ የማላውቀው ስልክ ተደወለልኝ እና ለጊዜው የከተማ ታክሲ ሥራ እንደተገኘልኝ ነግረው መጀመር እንደምችል አበሰሩኝ፤ አሁን የታክሲ ሥራ እየሠራሁ ቤቴን መምራት እና ልጆቸን ማስተማር ጀምሬያለሁ እግዚአብሔር ይመሥገን ዕድሜ ለጎረቤቶቸ በማለት ያሳለፉትን ከባድ የችግር ጊዜ አወሩን፡፡

እንደ ማሳያ የግለሰቡን ታሪክ አነሳን እንጅ በተነሱ ግጭቶች ምክንያት ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ሥራ መሥራት፣ በሰላም ወጥቶ መግባት ህልም እስኪመስል ድረስ እየተናፈቀ መጥቷል፡፡ ሰላም ምን ያክል ዋጋ እንዳለው የሚያውቀው ሰላም ያጣ ሰው ነው፤ በተለይ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ይሠሩ በነበሩ ዜጎች እና አሽከርካሪዎች ላይ የሚደርሰው እንግልት፣ ድብደባ፣ በጫኑት ጭነት ያለአግባብ በየቦታው ቀረጥ መቀረጥ እና ከሥራ መፈናቀል የተጎዱት ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ ምን ያህሎች የአካል እና የሥነ ልቦና ጉዳት ገጥሟቸዋል? በነሱ ስር ስንት ቤተሰቦች የችግሩ ሰለባ ሁነዋል? ልጆቻቸው በምን ሁኔታ ላይ ነው ያሉ? ስንቶች ትምህርታቸውን አቋርጠዋል? ይህን ቤት ይቁጠረው፡፡

እኛስ የዚህ ችግር ሰለባ የኾኑ እህት ወንድሞቻችን በአቅማችን እየደገፍን ይኾን ? ከላይ ታሪካቸውን የነገሩን ግለሰብ እና ቤተሰቡን ከችግር እንዲወጡ የታደጉ ጎረቤቶች ለሌሎቻችን አርዓያ ሊኾኑ የሚችሉ ናቸው፤ ቢያንስ አሁን እያሳለፍን ያለው ግጭት ተወግዶ የሰላም አየር ተንፍሰን ሁሉም ወደ ነበረበት እስኪመለስ በአካባቢያችን የሚገኙ የችግሩ ሰለባ የኾኑ ጉረቤቶቻችን በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ መጎብኘት መደግፍ እና ማገዝ ያስፈልጋል፡፡
ዋናው እና ትልቁ መፍትሄ ግን የክልሉን ሰላም መመለስ መኾን አለበት፤ ለዚህ ደግሞ ሁላችንም የበኩላችን ልንወጣ ይገባል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleትላልቅ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ መፈጸም ተችሏል።
Next article“አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በማረፋቸው የተሰማኝን ሃዘን እገልጻለሁ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)