ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ መፈጸም ተችሏል።

65

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ ቅድመ መደበኛ ጉባኤ ኮንፈረንስ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው። ኮንፈረንሱ “ከቃል እስከ ባሕል” በሚል መሪ ሀሳብ ነው እየተካሄደ ያለው። በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የክልል እና የዞን ከፍተኛ መሪዎች እየተሳተፉ ነው። በኮንፈረንሱ ላይ እንደሀገር የተከናወኑ ዐብይ የልማት ሥራዎች፣ የተስተዋሉ ፈተናዎች፣ ችግሮችን ለማለፍ የተወሰዱ መፍትሔዎች እና ለወደፊትም ሀገር እና ሕዝብን በብልጽግና መሰረት ላይ ለመትከል እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ይዳሰሱበታል። ከኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች መካከል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው በኮንፈረንሱ የሀገሪቱን ፈተና፣ ድል እና ተስፋ በጥልቀት በመመልከት ለሕዝብ ጠቃሚ የኾኑ ትልሞች ይገመገሙበታል ብለዋል። በመጀመሪያው የፓርቲው ጉባኤ ላይ የተቀመጡ የልማት እና መልካም አሥተዳደር አቅጣጫዎች አፈጻጸማቸው ምን ይመስል እንደነበርም ይፈተሻል ነው ያሉት።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሕዝብ ለ27 ዓመታት አማራነቱን ተቀምቶ የቆየ ነበር፤ አማራ ነኝ ብሎ ሲጠይቅም ዘርፈ ብዙ እንግልት ቢሲደርስበት ነበር፣ ከለውጡ በኋላ ግን የሕዝቡ የአማራነት ጥያቄ ተመልሷል ብለዋል። ሕዝቡ የወሰን እና ማንነት ጥያቄው መልስ አግኝቶለታል፤ በዚህም ደስተኛ ስለመኾኑ ገልጸዋል።

ዞኑ ከነጻነቱ ማግሥት የልቡ መሻት የኾነው ሰላም ተረጋግጦለታል ብለዋል። መልስ ያገኘው የወሰን እና ማንነት ጥያቄ በሕግ የጸና እና በዘላቂነት የተረጋገጠ እንዲኾ ደግሞ ሰላማዊ እና በእውነት ላይ ሥራ ያስፈልጋል ብለዋል። ሕዝቡ ሕጋዊ እና ሰላማዊ ጥያቄ ነው ያለው፤ እውነተኛ ማንነቱ ደግሞ ሰላማዊ በኾነ መልኩ በሕግ እንዲረጋገጥለት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
አቶ አሸተ እንዳሉት ዞኑ አሁን ላይ ሰላሙ የተጠበቀ፣ ሕዝቡም ለልማት የሚሠራ ነው ብለዋል። ታጥቀው በመንቀሳቀስ የዞኑን ሕዝብ ሰላም ለማወክ የሞከሩ አካላት ተከስተው ነበር፤ ይሁን እንጅ ሕዝቡ “በመስዋዕትነት የተገኘን ሰላም እንደገና ለማወክ መሞከር ነውር ነው” ብሎ መልሷቸዋል ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው።

የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ተለይተው ያደሩ ናቸው፤ እነዚህ ጥያቄዎች እንዲመለሱ ሰላማዊ መንገድ በመያዝ እና ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ሕዝቦች ጋር በጋራ መቆም ያስፈልጋል ነው ያሉት። የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሕዝብም ይህንን አምኖ በሰላም የሚንቀሳቀስ እና ሰላም ጠሎችን በንቃት የሚከላከል ሕዝብ ስለመኾኑ አቶ አሸተ ተናግረዋል።

ሌላው የኮንፈረንሱ ተሳታፊ የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በመጀመሪያው የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ ላይ የተቀመጡ አቅጣጫዎች ወደ መሬት ወርደው ያመጡትን ለውጥ ተመልክተናል ብለዋል። የሀገራችንን ብልጽግና የሚያረጋግጡ ትላልቅ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመኾኑም ተናግረዋል።
ለአብነትም ደብረ ብርሃን ከተማ ቀዳሚ የኢንዱስትሪ ማዕከል ኾና እንድትቀጥል ሰፊ ሥራ ተከናውኗል። ፓርቲው እየተከተለው ያለው የልማት አቅጣጫ ከተሞች እንዲስፋፉ፣ ለሀገራችን የእድገት ምሳሌ እንዲኾኑ እና ለነዋሪዎችም ምቹ እንዲኾኑ አስችሏል ብለዋል።
በኢኮኖሚያዊ፣ በማኅበራዊ እና በመልካም አሥተዳደር ዘርፎች ሕዝቡ ሲያነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎች እንዲፈቱ ተሠርቷል፤ በዚህ ረገድ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ሰብሮ ለመሻገርም ሰፊ ርብርብ ሲደረግ ቆይቷል፤ ውጤትም ተመዝግቧል ነው ያሉት።
በደብረ ብርሃን ከተማ እንደ ክልል የጸጥታ ችግር ገጥሞ ነበር፣ ጠንካራ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ በማከናወን የአካባቢውን ሰላም መመለስ ተችሏል ብለዋል። ሕዝቡ የሚፈልገው ሰላም እና ልማት ነው፤ አሁን ላይ ሰላሙን እየጠበቀ በመደበኛ ልማት ላይ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው በጉባኤው ላይ ብልጽግና ፓርቲ ያከናወናቸው የሀገር መሰረት የሆኑ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች እየተገመገሙ ነው፤ ተግዳሮቶች እና የመፍትሔ ሀሳቦችም እየተነሱ ነው ብለዋል።
ፓርቲው በርካታ ውጣ ውረዶችን እየተሻገረ ለሀገር ብልጽግና መሰረት የሚጥሉ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ እየጨረሰ ነው ብለዋል። ለአብነትም በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የሚከናወኑ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶችን አንስተዋል።
ተጀምረው የተጓተቱ የልማት ሥራዎች በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቁም ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ስለመኾኑ ገልጸዋል። የሀገር የልማት እና የብልጽግና ምልክት የኾነው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከገጠመው ውስብስብ ችግር ተላቅቆ ለፍጻሜ ለመብቃት መቃረቡ ፓርቲው ለልማት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ስለመኾኑም አቶ ቴዎድሮስ ጠቁመዋል።
ይፈጠር ከነበረው የአሠራር መጓተት በመላቀቅ፣ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ መፈጸም መቻል እና ሀገርን ማልማት የብልጽግና ፓርቲ ባሕል ኾኗል ብለዋል አሥተዳዳሪው።
በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ውስጥ ሕዝብ እና መንግሥት በመናበብ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመኾኑም ጠቅሰዋል።
ተፈጥሮ የነበረው የሰላም እጦት ችግር ተቀርፎ ሕዝቡ እፎይታ አግኝቷል፤ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አካላትን ከድርጊታቸው ተምረው ለሰላም እጅ እየሰጡ እየገቡ ነው ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሳምንቱ በታሪክ
Next articleወደ ልመና የወጣው አባት?