
✍የፊደል ገበታ አባት!
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከዕፅዋት ቀለም አንጥረው፣ ከሸምበቆ ብዕር ቀርፀው፣ የፍየል ቆዳ ፍቀውና አለስልሰው በመጽሐፍ “ሀ..ሁ… ዕውቀት ይስፋ፣ ድንቁርና ይጥፋ – ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ” የሚል መፈክር ተጠቅመው ወደ ማኅበረሰቡ ያዘለቁት “የፊደል ገበታው ጌታ” ቀኝ አዝማች ተስፋ ገብረ ሥላሴ ዘብሄረ-ቡልጋ የተወለዱት ሰሜን ሸዋ ቡልጋ ክታብ ወይራ አክርሚት ከተባለ ቀበሌ ነው፡፡
ከአባታቸው ከመምህር ገብረሥላሴ ቢልልኝ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ሥዕለሚካኤል ወልደአብ ታኅሣሥ 24 1895 በዚህ ሳምንት ነው የተወለዱት፡፡
“የፊደል ገበታ አባት” በሚል የሚጠሩት እኝህ ሰው በመጀመሪያ በብራና ላይ በእጃቸው እየፃፉ፣ በመቀጠልም በማተሚያ ቤት ማሽን እያባዙ ለሕዝብ እንዲደርስ አድርገዋል፡፡
ተስፋ ገብረስላሴ በ1909 ዓ.ም የ15 ዓመት ልጅ ኾነው ከትውልድ መንደራቸው ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ያረፉበት መንደር አራት ኪሎ ነበር፡፡
የተስፋ ገብረስላሴን የሥራ እና የሕይዎት ታሪክን ማዕከል አድርጎ የሀገሪቱን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ባሕላዊ ጉዳዮች በስፋት የሚያስስ “ዘመን ተሻጋሪ ባለውለታ” መጽሐፍ ተስፋ ገብረስላሴ የሕዝብ እና የሀገር ባለውለታ መኾን የቻሉት በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ አልፈው እንደኾነ ይገልጻል፡፡
ከኢጣሊያ ወረራ በፊት እና በኋላም ለእስር እና ውንጀላ ተዳርገዋል። በመጨረሻ ሁሉንም አሸንፈው በተደጋጋሚ ተሸላሚ ኾነዋል፡፡
በአፄ ኃይለስላሴ መንግሥት የቀኝ አዝማች ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበርም ደጋግሞ አመሥግኗቸዋል፡፡
✍”ብርሃንና ሰላም” ጋዜጣ ምሥረታ
በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን እና የጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የነበረው “ብርሃንና ሰላም” ጋዜጣ የተመሠረተው ታኅሣሥ 23 ቀን 1917 ዓ.ም ከ100 ዓመት በፊት ነበር፡፡
ብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት በ1914 ዓ.ም በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ መኖሪያ ግቢ ውስጥ ጨው ቤት በሚባለው ባለ ሁለት ክፍል ቤት ውስጥ ነበር ሥራውን የጀመረው፡፡
ታኅሣሥ 23 ቀን 1917 ዓ.ም ደግሞ ብርሃንና ሰላም የተባለውን ጋዜጣ ማተም ሲጀምር ስሙንም ከዚሁ ጋዜጣ ወረሰና “ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት” ተባለ፡፡
ይህም ማተሚያ ቤት ጋዜጦችን የማተም አገልግሎት እንዲሰጥ አስቻለው፡፡
ብርሃን እና ሰላም ጋዜጣ በ500 ቅጂዎች ያህል በሳምንት አንድ ጊዜ ሐሙስ ዕለት ይታተም እና የስርጭቱም ይካሄድ የነበረው በሁለት ፈረሰኞች አማካኝነት እንደነበር ታሪክ ያስረዳል።
የብርሃን እና ሰላም ጋዜጣ ስያሜን ስናይ የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋወራሽ ልዑል ተፈሪ መኮንን ባገራቸው ብርሃን እና ሰላም እንዲኾን ይፈልጉ ስለነበር ይህንን ጋዜጣ ብርሃን እና ሰላም ብለው እንደሰየሙትም ታሪክ ያስረዳል።
✍ ዲፕሎማቱ ኮፊ አናን
ሰባተኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን በመምራት የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ ናቸው።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊነት ሚና በዓለም ላይ ካሉ ፈታኝ የዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች አንዱ ነው።
እኝህ ታላቅ ሰው በ1938 በማዕከላዊ ጋና ነው የተወለዱት።
አናን በሥራቸው እና በጥረታቸው የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸንፈዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን በዋና ጸሐፊነት ከጎርጎሮሳዊው 1997 እስከ 2006 ባሉት ዓመታት መርተውታል።
ጋናዊው ዲፕሎማት የሶርያ ቀውስን ለመፍታት የተባበሩት መንግሥታት ልዩ ልዑክ ኾነውም ሠርተዋል።
በዓለማችን ላይ ተጋላጭ ለኾኑ ሕዝቦች የሚያሳዩት የቸርነት እና የመንፈስ ፅናት ብዙዎች ኮፊ አናንን የሚያስታውሱበት ኹኔታ ነው።
ዋና ጸሐፊም በነበሩበት ወቅት ከሳቸው በፊት ከነበሩም ኾነ ከሳቸው በኋላ ከነበሩ ኀላፊዎች በተለየ ወደ ጄኔቫ ይመላለሱ ነበር።
አናን ለተባበሩት መንግሥታት የሚዲያ አካል እንደተናገሩት የአሜሪካ እና የእንግሊዝ ጥምር ኀይል የኢራቅን ወረራ ሕገ ወጥ ማለታቸው የሰውየውን የውኃልክ የሚያሳይ ኾኖ ይጠቀሳል።
መልካም ስብእና ያላቸው ሰውም ነበሩ። ሰዎችን ለማውራት ጊዜ ባይኖራቸውም እንኳን ቆም ብለው ሰው ሰላም ይሉ እንደነበርም ይነገራል።
ኮፊ አናን በኮሶቮ የነበረው ጦርነትን ለማስወገድ ትልቅ ሚናን የተጫወቱ እና የአየር ፀባይ ለውጥ ለዓለም እንደ ስጋት መኾኑ እንዲታወቅ ሠርተዋል።
ኮፊ አናን የሚታወሱት በጦርነት ውስጥ ለሚማስኑ እና መሔጃ ላጡ፣ ለአካባቢ ቀውሶች እና በድህነት ውስጥ ተዘፍቀው ላሉ ምላሽን በመስጠት ነው።
በተደጋጋሚም ለዓለም መሪዎች ምንም ያህል ኀይል ቢኖራቸውም ከፖለቲካ ጥቅም በፊት ዜጎቻቸውን ሊያስቀድሙ እንደሚገባ በአጽንኦት ይናገሩ ነበር።
ታኅሣሥ 23 ቀን 1989 ዓ.ም ጋናዊው ዲፕሎማት ኮፊ አናን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰባኛው ዋና ፀሐፊ ኾነውም የተሾሙት በዚህ ሳምንት ነበር።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!