
ደሴ: ታኅሣሥ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የኮምቦልቻ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ያስገነባውን ሕንጻ የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ በተገኙበት አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የኮምቦልቻ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አሥኪያጅ ሰማን ዳውድ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ሕንጻ አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን፣ ለላቀ አፈፃፀም እና የቀጣናውን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማፋጠን አስተዋጽኦው የጎላ መኾኑን ገልጸዋል። የተቋማት መኖር ለከተማዋ ዕድገት እና ለኢንቨስትመንት ፍሰት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ያሉት የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ተወካይ ሙልጌታ ደርሴ ሌሎች ተቋማትም ከተቋሙ ልምድ ሊወስዱ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ “ሀገራችን ካሉባት ስብራቶች አንዱ የተቋማት ስብራት ነው” ብለዋል። ኮሚሽነሩ የሚገነባው ተቋም ስብራቷን ጠግኖ ለውጤት ማብቃት አለበት ነው ያሉት። ኮሚሽነሩ ለሥራ ምቹ ከባቢ መፍጠር ገቢን ለማሳደግ እና ለውጤታማነት አስተዋጽኦው የጎላ ነው ብለዋል።
የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ “ሀገራችን ኢትዮጵያ አንገቷን ቀና እንድታደርግ፣ ወደ ገናናነቷ እንድትመለስ፣ የልማት ሥራዎች እንዲከናወኑ እና ኢኮኖሚያችን እንዲዳብር አስተማማኝ የገቢ አቅም ሊኖረን ይገባል” ብለዋል ሚኒስትሯ ሕንጻውን መርቀውም ሥራ አስጀምረዋል።
ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የተሻለ ገቢ መሠብሠብ የተቻለ ቢኾንም የመንግሥት ትልቁ ኀላፊነት ነገን የተሻለ ማድረግ በመኾኑ በተሻለ ትጋት መሥራት እንደሚገባ ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮምቦልቻ ቅርንጫፍ አስገንብቶ ያስመረቀው ባለ ስድስት ወለል ሕንጻ 500 ሚሊዮን ብር ወጭ የተደረገበት መኾኑን ለማወቅ ተችሏል።
ዘጋቢ:- አበሻ አንለይ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!