ኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል ኢትዮጵያን ጉዞ ለማሳካት ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገለጸ።

46

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር) ከኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ጋር የኢትዮጵያን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለማፋጠን በጋራ መሥራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

ሚኒስትሩ ኢትዮ ቴሌኮም የሀገር ኩራት እና ምልክት መሆኑን በመግለጽ ፤ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ግንባር ቀደም ሚና በመጫወት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ተቋሙ በዲጂታል አገልግሎቶች እና በቴሌብር አስደማሚ ውጤት በማስመዝገብ ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ የዲጂታል አገልግሎት ተደራሽነት እና አካታችነትን በመጨመር ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ በሚያስችሉ ዘርፎች ላይ በቅንጅት እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በበኩላቸው ፤ ኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል ኢትዮጵያን ጉዞ ለማሳካት ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢኖቪሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች የኢትዮ ቴሌኮምን ኤክስፒሪየንስ ማዕከል የጎበኙ ሲሆን፣ የስማርት ሲቲ ፕሮጀክትን ጨምሮ እንደ ግብርና፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ትራንስፖርት፣ ፋይናንስ እና ቱሪዝም ያሉ ዘርፎችን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ግዙፍ አቅም መገንባቱን አረጋግጠዋል፡፡

ተቋማቱ የዲጂታል ኢትዮጵያ ትራንስፎርሜሽንን ለማፋጠን ቋሚ የጋራ መድረክ በመፍጠር በቅርበት ለመሥራት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ከኢትዮ ቴሌኮም የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleቻት ጂፒቲ ምንድን ነው ? (ሳይቴክ ዘመነኛ)
Next articleወቅታዊ መረጃ !