“ኑ በዓለ ልደትን በቅዱስ ላሊበላ እናክብር፤ የበረከቱ ተከፋይም እንሁን” ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ

51

ወልድያ: ታኅሣሥ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል እና የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ለልደት በዓል መልዕክት አሥተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም “በመላው ዓለም ለምትገኙ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች እንኳን ለጌታችን፣ ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ” ብለዋል።

በደብራችን በቅዱስ ላሊበላ እናንተን ለመቀበል ሁሉንም ሃይማኖታዊ ዝግጅት አከናውነናል፣ ቤተክርስቲያናችን መንፈሳውያን ልጆቿ ሲመጡ እግር በማጠብ ትቀበላለች ነው ያሉት።

ቤተክርስቲያን ሁሉንም ሃይማኖታዊ ዝግጅት ስላደረገች ከየትኛውም የዓለም ክፍል ያላችሁ ወገኖቻችን እግዚአብሔር በፈቀደላችሁ ልክ መጥታችሁ አብረን የጌታችን፣ የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን በቅዱስ ላሊበላ እንድናከብር ጥሪያችን ይድረሳችሁ ብለዋል።

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ዓለም አቀፍ በዓል ነው፣ በመላው ዓለም ያሉ ክርስቲያኖች እንደየ ሀገራቸው የዘመን አቆጣጠር ያከብሩታል ያሉት ብፁዕነታቸው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንም በመላ ሀገሪቱ በድምቀት ይከበራል፣ በቅዱስ ላሊበላ ደብር ደግሞ ከሌላው ደመቅ ብሎ ይከበራል ነው ያሉት።

የጌታ አገልጋይ ባለሟል ቅዱስ ላሊበላ ክርስቲያን ወገኖቻችን የጌታችን የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ሊያከብሩ እንደሚያጓዙ ያውቅ ነበር፤ ብዙዎቹ በህመም እና በእርጅና መሄድ እያቃታቸው ከበረከቱ ተከፋይ መኾን ሳይችሉ ሲቀሩ አይቷልና በኢትዮጵያ ኢየሩሳሌምን የሚተካ ዳግማዊት ኢየሩሳሌምን ገንብቷል ብለዋል።

ወደ ቅዱስ ላሊበላ ደብር የመጣ፣ የተሳለመ፣ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ያከበረ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በቤተልሔም እንደተሳለመ ስለሚቆጠርለት ልደት በቅዱስ ላሊበላ ደብር ከሌሎች በበለጠ ደምቆ ይከበራል ነው ያሉት።

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ባለሟል የቅዱስ ላሊበላም የልደት በዓል ታኅሣሥ 29 በመኾኑ ተጨማሪ በዓል ነው፣ ጌታችን በመታዘዝ እና በማገልገል አርዓያ እና ምሳሌ የኾነን የቅዱሱ ልደት በዚሁ ቀን ይከበራልና በዓሉ ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ መልኩ ደምቆ እና ገንኖ ይከበራል ብለዋል።

ሁኔታዎች የፈቀዱላችሁ ሁሉ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ እና የባለሟሉን የቅዱስ ላሊበላ በዓለ ልደትን በአንድ ቀን፣ በአንድ ቦታ እንድናከብር ጥሪ እናቀርብላችኋለን ብለዋል።

በቀደመው ዘመን ኢትዮጵያውያን ለወራት ተጉዘው የልደትን በዓል በኢየሩሳሌም በቤተልሔም ያከብሩ እንደነበር የተናገሩት ብፁዕነታቸው ቅዱስ ላሊበላ ዳግማዊት ኢየሩሳሌምን ሲያዘጋጅም የትራንስፖርት አማራጭ አልነበረም፣ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሃይማኖት ተከታዮች በእግራቸው እየመጡ ነው ሲያከብሩ የነበሩት ብለዋል።

በመድከማቸው፣ በመንከራተታቸው፣ የሚያገኙት ጸጋ እና ክብር አለ፣ ምክንያቱም አምላካቸውን በመውደድ የሚደረግ ስለኾነ ነው ብለዋል። ዛሬም ቢኾን የትራንስፖርት አማራጮች እያሉ ብዙ ኢትዮጵያውያን በእግራቸው ወደ ቅዱስ ላሊበላ እንደሚመጡ ነው የተናገሩት።

መውጣት እና መውረዳቸው በአምላካቸው ፊት ዋጋ እንደሚያስገኝ ስለሚያምኑ ነው፣ በቤተክርስቲያን ደግሞ ታምኖ የተከፈለ ዋጋ ሁሉ ሰማያዊ ዋጋ ያስገኛል ነው ያሉት።

ብዙ ወገኖች በእግራቸው ተጉዘው ላሊበላ እየተገኙ ነው በዚህም የስጋ እና የነፍስን በረከት እንደሚያገኙ እናምናለን ብለዋል። በእግር መምጣት የማትችሉትም ደግሞ በትራንስፖርት ተጉዛችሁ አብረን እናክብር ነው ያሉት።

አብረን ብናከብር የበረከቱ ተከፋይ እንኾናለን ብለዋል ብፁዕነታቸው በመልዕክታቸው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መልዕክት፦
Next articleየምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ መልእክት!