
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በከተሞች የሚታየውን የሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት ከመደበኛ የሥራ ዕድል ፈጠራ ባለፈ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በሀገሪቱ በሚገኙ አሥር ከተሞች እየተሠራ ይገኛል። በአማራ ክልል ተጠቃሚ ከኾኑ ከተሞች ውስጥ ደግሞ ባሕር ዳር፣ ጎንደር እና ኮምቦልቻ ይገኙበታል። በባሕር ዳር ከተማ ብቻ በሁለት ዙር ሥልጠና ከ2 ሺህ 700 በላይ የሚኾኑ ወጣቶች የሥራ እድል ተጠቃሚ ኾነዋል።
የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ከኾኑ ወጣቶች ውስጥ ደግሞ ስመኘው ታከለ ይገኝበታል። ወጣት ስመኘው እንደነገረን በተለያዩ ምክንያቶች ስድስተኛ ክፍል ነበር ትምህርቱን ያቋረጠው። ይሁን እንጅ በ“ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም›› ለስድስት ወራት የጣውላ ሥራ በመሠልጠኑ በአንድ ድርጅት የሥራ እድል ተፈጥሮለት እየሠራ ይገኛል።
በቀጣይ ከራሱ ባለፈ ለሌሎች ወጣቶች ጭምር የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችል ድርጅት የማቋቋም ህልም እንዳለው ነግሮናል። የጁኒዬር ጋርመንት እና የፋሽን ተቋም ሥራ አሥኪያጅ ሙሉጌታ ውለታው በአንደኛ ዙር ‹‹ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም ›› ለሠለጠኑ 48 ወጣቶች፣ በሁለተኛው ዙር ደግሞ ለ46 ወጣቶች ቋሚ የሥራ እድል በመፍጠር የአንደኛ ደረጃ ተሸላሚ ኾነዋል ብለዋል።
የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች በሽመና፣ በጥልፍ እና በልብስ ስፌት በድርጅቱ የሠለጠኑ ናቸው። ሌሎች ድርጅቶችም ባላቸው ክፍት ቦታ ወጣቶችን አሠልጥነው ወደ ሥራ ማሠማራት ቢችሉ ለወጣቶች የሥራ እድል ከመፍጠር ባለፈ በሀገሪቱ ያለውን የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስም አቅም ይኾናል ብለዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ ኀላፊ ዘመነ አሰፋ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በአንደኛ ዙር ‹‹ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም›› ለ1 ሺህ 369 ወጣቶች የሥራ እድል ተፈጥሯል ብለዋል። በሁለተኛው ዙር ደግሞ በከተማ አሥተዳደሩ የሚገኙ 286 የግል ድርጅቶች 1 ሺህ 366 ወጣቶችን ለስድስት ወር አሠልጥነው እንዲቀጠሩ ተደርጓል ነው ያሉት።
መርሐ ግብሩ በክልሉ መጀመሩ በከተማ አሥተዳደሩ የሚገኙ የግል ድርጅቶች ያላቸውን ክፍት ቦታ ለማወቅ ተችሏል። መንግሥት እና ድርጅቶች እንዲተሳሰሩ እድል ፈጥሯል። የሚፈጠረው የሥራ እድል ቋሚ መኾኑ እና 12ኛ ክፍል እና ከዚያ በታች የትምህርት ደረጃ ያላቸው እና የሥራ ዕድል ያልተፈጠረላቸው ወጣቶች ላይ ማተኮር መቻሉ ሌላው መልካም አጋጣሚ መኾኑን ነው ያነሱት።
ሌሎች ድርጅቶችም ባላቸው ክፍት ቦታ የሥራ እድል በመፍጠር ሀገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቀርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!