
ሁመራ: ታኅሣሥ 25/04/17 ዓ.ም (አሚኮ) “ያገኘነው ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ሥልጠና የአካባቢያችንን ሰላም ለመጠበቅ ያስችለናል” ሲሉ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በዳንሻ ከተማ የ2ኛው ዙር ተመራቂ ሚኒሻዎች ተናግረዋል። ከተመራቂዎቹ መካከል መቶ አለቃ ልጁ ካሳ ይመር
አካባቢያቸው የተጠናከረ የሰላም ሥራ እንደሚያስፈልገው የገልጸዋል።
“በቂ የሆነ የአመለካከት እና የግንዛቤ ትምህርት አግኝተናል” ያሉት መቶ አለቃው ከሥልጠናው ያገኙት ዕውቀት የአካባቢያቸውን ሰላም መጠበቅ እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል። የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ለድርድር እንደማይቀርብ ከግምት ውስጥ በማስገባት ያገኘነውን ሰላም ለማጽናትም ግንዛቤ ተፈጥሮልናል ያሉት ደግሞ ሌላኛው ተመራቂ አቶ አጥናፉ ጎበዜ ናቸው።
ከግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቱ በተጨማሪ ልዩ ልዩ ወታደራዊ ሳይንስ መሠልጠናቸው አካባቢያቸውን ለመጠበቅ አቅማቸውን እንዳሳደገላቸው አቶ አጥናፉ ገልጸዋል። “እናንተ የተከዜ ዘብና የሰላም አርበኛ ናችሁ፤ እናንተ ባላችሁበት ሁሉ ሕዝቡ በሰላም ወጥቶ ይገባል” ያሉት ደግሞ የዞኑ ብልጽግና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዋኘው ደሴ ናቸው።
ከሕግ ውጭ ሆኖ ለሚንቀሳቀስ ማንኛውም አካል የሕዝብን ሰላም ለመጠበቅ የተመራቂዎች ተልዕኮ ከፍተኛ መኾኑንም አቶ ዋኘው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። ሁሉም ሰው ሠልጥኖ አካባቢውን ሲጠብቅ እና ችግሮችን ሲፈታ የመከላከያ ሠራዊቱ አጋዥ ይሆናል ያሉት ደግሞ በሀገር መከላከያ ሠራዊት የ5ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ሚልኬሳ ረጋሳ ናቸው።
የዚህ ሥልጠና ዋና ዓላማም የአካባቢውን ሰላም በራስ አቅም ለመጠበቅ ለማስቻል እንደሆነ ጄኔራሉ ተናግረዋል። በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የ5ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ብራጋዴር ጄኔራል ሚልኬሳ ረጋሳ፣ የዞኑ የብልጽግና ጽሐፈት ቤት ኀላፊ ዋኘው ደሴ፤ የዞኑ የሚሊሻ መምሪያ ኀላፊ ክብረአብ ስማቸው እና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!