
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 25/2017 ዓ.ም የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ከተማ ልማት ቢሮ ከአሚኮ ዘጋቢዎች ጋር አምራች ኢንዱስትሪዎች ያሉበትን ኹኔታ ቅኝት አድርጓል። በጉብኝቱ በዩኒሰን የምግብ ዘይት ፋብሪካ እና ማርታ ምግብ ኮምፕሌክስ ምልከታ ተደርጓል። በዩኒሰን የምግብ ዘይት ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ፀሐዬ አበራ ፋብሪካው ባለፉት ሁለት ዓመታት የምግብ ዘይት እና ሌሎች ምርቶችን በማምረት ለኅብረተሰቡ እያደረሰ መኾኑን ገልጸዋል።
በቀን እስከ 70 ሺህ ሊትር ዘይት የማምረት አቅም እንዳለው እና በክልሉ ተደራሽ ለመኾን እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። በውጪ ምንዛሪ የሚገቡ እቃዎች እና የአኩሪ አተር ዋጋ መጨመር ፈተና መኾኑን ገልጸዋል። በዩኒሰን ቢዝነስ ግሩፕ ጄኔራል ማናጀር አሻግሬ ጌትነት ከልደት በዓል ጋር በተያያዘ ለሚኖረው ፍላጎት የምርት ጭማሪ አድርገን እስከ ጎንደር ድረስ እየላክን ነው ብለዋል።
አቅርቦቱ በመኖሩም የዋጋ መረጋጋት መፍጠሩን ጠቅሰዋል። አከፋፋዮች በተጋነነ ዋጋ እንዳይሸጡ የፋብሪካውን ሱቅ በመክፈት በተተመነ የችርቻሮ ዋጋ እየሸጠ መኾኑንም ገልጸዋል። ፋብሪካ ላይ እና ገበያ ላይ የሚሸጥበት የዋጋ ልዩነት 10 ብር ብቻ በማድረግ የዋጋ ንረት እንዳይኖር በመቆጣጠር እየሠሩ መኾኑን ጠቅሰዋል።
የማርታ የምግብ ኮምፕሌክስ ሥራ አስኪያጅ በአምላኩ የኔነህ ፋብሪካቸው ምግብ ነክ ምርቶችን እያመረተ መኾኑን ገልጸውዋል። የሥራ ዕድል በመፍጠርም ኾነ ገበያ በማረጋጋት እየተሳተፈ መኾኑን ተናግረዋል። ምርቶችን ለሸማቾች ማኅበር በማቅረብ ለዋጋ መረጋጋትም እየሠራን ነውም ብለዋል። በቀን 824 ኩንታል የምግብ ዱቄት የማምረት አቅም ቢኖረንም በግብዓት እጥረት በቀን በ410 ኩንታል ብቻ ተወስነናል።
የልደት በዓል የምርት አጥረት እንዳይፈጠር በቂ ምርት እያመረቱ እንደኾነ ገልጸዋል። በአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ የኢንዱስትሪ ምርት ውጤታማነት ተወካይ ዳይሬክተር ይናገር ይላቅ በአማራ ክልል ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ 854 አምራች ኢንዱስትሪዎች አሉ ነው ያሉት።
ከነዚህ ውስጥም በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙ 101 የምግብ ዱቄት እና 57 የምግብ ዘይት ፋብሪካዎች ናቸው ብለዋል።
በየዓመቱ በአማካይ እስከ 80 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ይፈጠራሉ፤ ቢሮው የመሰረተ ልማት፣ የገንዘብ፣ የሊዝ፣ የግብዓት እና የቁሳቁስ ችግሮቻቸውን ለመፍታት እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። የማምረት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የ2016 በጀት ዓመት ግምገማም የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም 62 በመቶ ደርሷል ነው ያሉት። ዘንድሮ 65 በመቶ ለማድረስ እና ተኪ ምርት እንዲያመርቱ፣ ለውጭ ምርት እንዲያመርቱ እና የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ታስቦ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
ቢሮው አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለኅብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል። መሰረተ ልማት በማሟላት፣ በግብዓት እና ብድር አቅርቦት፣ ኢንቨስትመንትን ያበረታታል ብለዋል። አሁን ላይ የዋጋ እንጂ የምርት ችግር እንደሌለም ጠቅሰዋል። በኢትዮጵያ ታምርት ቢሮው ኢንዱስትሪዎችን በማገዝ የተሻለ ምርት እንዲመረት እየሠራን ነው ብለዋል።
ከባንኮች ጋር በመወያየት የብድር አቅርቦት በማመቻቸት እየተሠራም ነው ብለዋል። በተያዘው በጀት ዓመትም ኢንዱስትሪዎች ከ3 ቢሊየን ብር በላይ ተጠቃሚ ኾነዋል። ፋብሪካዎች የሥራ እድል እንዲፈጥሩ እና በብዛት እንዲያመርቱ የማስፋፊያ ቦታ በመስጠት፣ መሰረተ ልማት በማሟላት እየታገዙ ነውም ብለዋል።
በበዓልም ኾነ በአዘቦት ኅብረተሰቡ በምርት እጥረት እንዳይቸገር ኢንዱስትሪን ከኢንዱስትሪ በማስተሳሰር፣ ግብዓቶችን እንዲያገኝ እና እንዲያመርቱ እየተደረገ መኾኑን አሳውቀዋል። ለበዓልም ተጨማሪ ምርት እንዲመረት እና ወደ ገበያው እንዲያሰራጩ መደረጉንም አንስተዋል። ከውጪ የሚመጡ ምርቶችን የሚተኩ ምርቶች እንዲያመርቱ በማድረግም እየተሠራ መኾኑን ተወካይ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
        👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
            
		