“እንኳን አየውህ ሳይደክም ጉልበት የት አገኝህ ነበር ከዋልኩኝ ከቤት”

35

ወልድያ: ታኅሣሥ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሠርክ አዲስ የኾኑትን፣ ታይተው የማይጠገቡትን፣ ሲያዩዋቸው የሚያሳሱትን፣ ሲርቋቸው የሚናፍቁትን፣ የሥልጣኔ ልክ ማሳያዎችን፣ የታላቅነት ምስክሮችን፣ የጠቢብነት አብነቶችን፣ የቀዳሚነት አሻራዎችን አይቶ የማይገረም ማነው? አይቶ የሚጠግባቸው፣ ተረድቶ የሚጨርሳቸው፣ ጽፎ የሚገልጻቸው፣ ተናግሮ የሚፈጽማቸውስ ከየት ይገኛል? ሁሉም እነዚህስ ረቂቆች ናቸው እያለ ያልፋቸዋል እንጂ።

ቅድስና የሠራቸው፣ ብፅዕና ያስዋባቸው፣ ረቂቅ ጥበብ ያበጃጃቸው፣ የሰማይ ምስጢር የተገለጠባቸው፣ ሰማያዊት እና ምድራዊት ኢየሩሳሌም የሚነበቡባቸው፣ ሰውና መላእክት ኅብረት የፈጠሩባቸው፣ በኀብረት ያነጿቸው ፣ በኅብረትም የሚዘምሩባቸው፣ የፈጣሪ እጆች ያረፉባቸው፣ ግርማው የማይለያቸው፣ ሞገሱ የማይርቅባቸው ናቸው።

እነዚህ ረቂቅ ሥራዎች ምሥጋና አይታጎልባቸውም፣ ውዳሴ አይቋረጥባቸውም፣ ይልቅስ በሠርክ ምልጃ ይቀርብባቸዋል። ለምድር ረድኤት እና በረከት ይለመንባቸዋል። ሰላም እና ፍቅር ይበዛ ዘንድ ይጸለይባቸዋል ረቂቆቹ የቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናት። በዚህች ሥፍራ በረከትን የሚሹ፣ ታሪክን ለማወቅ የሚጓጉ፣ ሃይማኖትን ለመማር የሚፈልጉ፣ ጥበብን ለማድነቅ የሚነሱ ሁሉ ይሠባሠቡባታል። በአጸዷ ሥር በጋራ ኾነው ይደነቁባታል።

“ደስ አያሰኙም እምትላቸው ዘመኖች እና ወራቶች ሳይመጡ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ” ተብሎ እንደተጻፈ ክርስቲያኖች በጉብዝና ወራታቸው አምላካቸውን ወደሚያስቡባት ሥፍራ ወደ ላሊበላ ይጓዛሉ። በተለይም የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በደረሰ ጊዜ በረከትን፣ ረድኤትን እና ጽድቅን ያገኙ ዘንድ አቅም ያላቸው በእግራቸው፣ ደከም ያሉት በመጓጓዣ ታግዘው ወደ ላሊበላ ያቀናሉ። በደረሱም ጊዜ:-

” ዓይኔ ዓለም አየ እግሬ ደርሶ
የድንጋይ ወጋግራ የድንጋይ መሰሶ” እያሉ እጹብ ኾኖ የተሠራውን ያደንቃሉ። ይገረማሉም።

በቅዱስ ላሊበላ ገድል “ዓይናችን ሳይደክም፣ ልባችን ሳይደነዝዝ፣ ወደ ታላቂቱ የቅዱሳን ከተማ ግዑዝ አለት በፈጣሪው ትዕዛዝ ለፍጡር ወደ ተገዛበት ደብረ ሮሃ ይምጡ። ቅድስቲቱን ከተማ የኢየሩሳሌም ሰማያዊት ምሳሌ ታንጻ ታገኟታላችሁ። የቃል ኪዳን፣ የምሕረት፣ የበረከት፣ የምሥጋና እና የምልጃ ዝናብ የሚወርድባትን የቤዛ ኩሉ ዓለም በረከት በእርሷ ብቻ የሚታይባትን፣ ሰማያዊ እና ምድራውያን የሚዘምሩባትን ከተማ ታዩ ዘንድ ኑ” ተብሎ ተጽፏል።

ለበረከት የተጉ አማኞችም በቅድስቲቱ ምድር ተሠባሥበዋል። ከጎንደር አንዳቤት ተጉዘው በላሊበላ በቤተ ጊዮርጊስ ሲዘምሩ ያገኘናቸው አባ መላክ ዓለማየሁ ለአምስተኛ ጊዜ መጥቻለሁ ነገር ግን ጊዜው ሲደርስ ላሊበላ ይናፍቀኛል። አዲስም ይኾንብኛል ይላሉ።

ከእርሳቸው ጋር የተገናኘነው:-
” እንኳን አየውህ ሳይደክም ጉልበት

የት አገኝህ ነበር ከዋልኩኝ ከቤት” እያሉ እየዘመሩ በቤተ ጊዮርጊስ ምሥጋና እያቀረቡ ባለበት ጊዜ ነበር። ዝማሬዎች ልብን ይሠርቃሉ። ጀሮም ለመስማት ታዘነብላለች። አዎን ከጉልበት ሳለሁ አየሁት እንጂ ደክሜ ከቤት ብውልማ የት አገኘው ነበር፤ ሳይደክም ጉልበቴ ስላገኘሁት ደስ ተሰኘሁ፤ አምላኬንም አመሠገንኩት ነው ያሉት።

እዚህ የማመሠግነው ሳየው ደስ እያለኝ፣ ዓመቱ ሲደርስ እየናፈቀኝ ነው ይላሉ። ዓመት ሲደርስ ያላዩትን ኑ እያልኩ እየያዝኩ እየመጣሁ ነው ብለውናል። 80 ዓመታቸው ላይ የሚገኙት አባ መላክ አቅሜ ስለደከመ በእግሬ መምጣት ባይቻለኝም በቃ እስኪለኝ ድረስ ግን ምድሩን እየረገጥኩት እኖራለሁ። ዞሮ ዞሮ ከቤት፣ ኖሮ ኖሮ ከሞት እንደተባለ ሞቴ ስለማይቀር ነፍሴን እንዲታደጋት እመጣለሁ ነው ያሉን።

“እኔ ያየሁትን ካላያችሁ እንደተፈጠራችሁ አትቁጠሩት፤ እየመጣችሁ እዩት፤ ይሄ የድንጋይ ወጋግራ፣ የድንጋይ መሰሶ ያለበት ድንቅ ሥፍራ ነው። የላሊበላን ሕንጻ ቤተክርስቲያን ያላየ እንደተፈጠረ አይቆጠርም፤ ላሊበላ በጎጆ የተቀለሰ አይደለምና” ይላሉ። ከአባ መላክ ጋር አብረው ላሊበላ የመጡት ሞላ አሰፋ ባየሁት ነገር ደስታዬ ወደር የለውም ነው ያሉት። “ይሄን ያላየ ሰው አለሁ አይበል፤ የለምና፤ የላሊበላ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ድንቅ ነው፤ የትም የለም” ይላሉ።

ይህን ቦታ ቢቻልስ በሠርክ ባይኾን ግን በልደት ቀን ማየት ይገባል ነው ያሉት። “ወደዚህ ሥፍራ የምመጣው ዕድሜ እንዲሰጠኝ፣ ጤናዬን እንዲጠብቅልኝ እና መቼም ሰው ነኝና በደል መሥራቴ አይቀርም በሞትኩ ጊዜ ነፍሴን ይቅር እንዲላት ነው” ይላሉ።

“ወድቄ ነበር ከዛፍ ላይ
አሞራ ይመስል ሥጋ ሥጋ ሳይ” እያሉ እሳቸውም በአጸዱ ሥር ያዜማሉ። ስጋን ብቻ ማየት ይጥላል፤ ነፍስንም ማየት መልካም ነውና፤ ላሊበላ የምመጣው ለነፍሴ ነው ብለዋል።
ክርስቲያኖች ረጅሙን መንገድ እየተጓዙ ቅዱስ ላሊበላ ሲደርሱ ለአምላካቸው እንዲህ ይላሉ:-
” አያወላውልምይመራኛል፣ አያወላውልምይምረኛል፣
የላስታን አቀበት ስወጣው አይቶኛል”

ያን ሁሉ መንገድ አቆራርጠው፣ ውኃ ጥሙን እና ረሃቡን ችለው፣ ውርጭ እና ሀሩሩን ተቋቁመው፣ ቁልቁለቱን ወርደው፣ አቀበቱን ወጥተው በተቀደሰው ሥፍራ የሚደርሱት በረከትን እና ጽድቅን ለማግኘት ነው። አምላካቸውም የልባቸውን መሻት እንደሚፈጽምላቸው ያምናሉ።

ጉልበት ሳይደክም ድንቁን ሥፍራ ተመልከቱት። ከቤት ሳትውሉ ረቂቁን ነገር እዩት። ተመላለሱበት። ከቤት በዋላችሁ ጊዜ ይሄን ለማየት ብትሹ አታገኙትምና። የጉብዝናችሁ ዘመን ሳያልፍ ወደ ቅዱስ ላሊበላ ገስግሱ። በተቀደሰችው ሥፍራም ድረሱ። በዚያች ሥፍራ ረቂቅ ነገር ሞልቷልና።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Amhara Media Corporation | Instagram, Facebook, TikTok | Linktree

Previous articleየአማራ ሴቶች ማኅበር ተዛብቶ የቆየውን የሥርዓተ ጾታ አስተሳሰብ እና ተግባር ለማስወገድ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከቱ ተጠቆመ።
Next articleለልደት በዓል የምርት እጥረት እንዳይኖር በብዛት እያመረቱ መኾኑን አምራች ኢንዱስትሪዎች ገለጹ።