
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጥላ የበጎ አድራጎት ማኀበር ከባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ጋር በመተባበር በባሕር ዳር ከተማ “ንቂ ኢትዮጵያ” በሚል መሪ መልዕክት የመጽሐፍት ዐውደ ርዕይ እያካሔደ ነው። ማኅበሩ እርዳታ የሚሹ ወገኖችን ከማገዝ በተጨማሪ ንቁ ዜጋ ማፍራት ላይ በትኩረት የሚንቀሳቀስ ማኅበር ነው።
የአራተኛ ዓመት የኮሌጅ ተማሪ እና የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ወጣት ሰናይት ወርቁ ማኀበሩ ከስድስት በላይ በጎ ተግባራትን አንግቦ እየተንቀሳቀሰ ያለ ማኅበር ነው ብላለች። ማኅበሩ ከተግባራቶቹ ውስጥ ንቁ ዜጋ መፍጠር ዋና ዓላማው እንደኾነም ገልጻለች። እኛ ኢትዮጵያውያን በተለይ ወጣቱ በንቃት ሊተገብራቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ ነው ያለችው። ፕሬዚዳንቷ አስተዋይ እና ታሪኩን የሚያውቅ አንባቢ ትውልድን መገንባት ላይ ማተኮር እንደሚገባም ነው ያስገነዘበችው።
ያለፈውን ታሪክ ለመገንዘብ እና ነገን ለመሥራት ማንበብ ትልቅ መፍትሔ ነውም ብላለች።  ለሁለተኛ ጊዜ የተከፈተው የመጽሐፍት ዐውደ ርዕይም ትውልዱ ማንበብን ባሕሉ እንዲያደርግ ለማነሳሳትም እንደኾነ ገልጻለች። በመጽሐፍት ዐውደ ርዕዩ መክፈቻ ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ጋሻው እንዳለው ትውልዱ ማንበብ ላይ መዝመት እንዳለበት ተናግረዋል።

ዘመናዊ ትምህርት ሳይኖር አባቶች ይራቀቁበት የነበረውን ዕውቀት ማንሳት እና መፈተሽ ከትውልዱ ይጠበቃልም ነው ያሉት። ከማንበብ ጥቅም እንጅ ጉዳት የለም ያሉት ኀላፊው በተፈጥሮ ጸጋ የታደለችው ባሕር ዳር ከተማ የማንበብ ባሕልም ሊዳብርባት ይገባል ብለዋል። የተከፈተው የመጽሐፍት ዐውደ ርዕይ ዋና ዓላማው የማንበብን ትርጉም ለማነቃቃት እንደኾነም ገልጸዋል።
ባለፉት አስርት ዓመታት ሥነ ጽሑፍ እና ጥበብ እንዳያድግ ተዘምቶበት መቆየቱንም አንስተዋል። ለማወቅ ትልቅ ትርጉም ሊሠጠው እንደሚገባም አሳስበዋል። “ታሪካችን በውል የምንገነዘብ አንባቢ ትውልዶች ልንኾን ይገባል” ነው ያሉት። ባሕር ዳር ከተማ የዕረፍት ማሳለፊያ ናት ያሉት ኅላፊው ወደ ከተማዋ የመጣ ሁሉ የመጽሐፍት ዐውደ ርዕዩ ላይ ጎራ በማለት የበጎ ዓላማው ተካፍይ እንዲኾንም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የመጽሐፍት ዐውደ ርዕዩ በባሕር ዳር ከተማ ዘንባባ መናፈሻ በይፋ የተከፈተ ሲኾን ከታኅሣሥ 25 እስከ 27/2017 ዓ.ም ድረስ እንደሚቆይም ተገልጿል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
        👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
            
		