
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በመደበኛ የሥራ ዕድል ፈጠራ ከሚከናወኑ ተግባራት ጎን ለጎን ከዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መርሐ ግብሮች እየተከናወኑ መኾኑን የሥራ እና ሥልጠና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ከመርሐ ግብሮች መካከል አንዱ ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር  እየተተገበረ የሚገኘው “ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም” አንዱ ነው፡፡
ፕሮግራሙ በከተሞች የሚገኙ ከ18 እስከ 25 ዓመት የዕድሜ ክልል ያላቸው፣ የትምህርት ደረጃቸው ደግሞ ከ12ኛ ክፍል እና ከዚያ በታች የሚገኙ ወጣቶችን የሥራ ዕድል መፍጠር ዓላማ ያደረገ ነው። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ “ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም” ከጀመረ ጀምሮ የወጣቶችን የሕይዎት ክሕሎት ሥልጠና ከተሰጠ በኋላ በተለያዩ ድርጅቶች የሥራ እድል እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል። ይህም በከተማ አሥተዳደሩ በመደበኛነት እየተሠራ ያለውን የሥራ ዕድል ፈጠራ እየደገፈ ይገኛል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ኀላፊ  ስቡህ ገበያው (ዶ.ር) በ2016 ዓ.ም በ“ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም” 1 ሺህ 369 ወጣቶች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል። በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በተደረገው ውድድርም ባሕር ዳር ከተማ አሸናፊ መኾኑን ገልጸዋል።
በዚህ ዓመትም 1 ሺህ 366 ወጣቶች የተመረቁ ሲኾን ወጣቶቹ በሚሠማሩበት የሥራ ዘርፍ የወጣትነት ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም ከራሳቸው አልፈው ለሀገራቸው አሻራ እንዲያሳርፉ አሳስበዋል።
የሥራ እና ሥልጠና ሚኒስቴር የሥራ ሥምሪት እና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ሰለሞን ሶካ መንግሥት በቀዳሚነት ከያዛቸው ሥራዎች ውስጥ በከተሞች በስፋት የሚስተዋለውን የወጣቶች የሥራ አጥነት ቁጥር መቀነስ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከመደበኛነት ባሻገር ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለወጣቶች የሥራ ዕድል እየተፈጠረ ይገኛል ነው ያሉት።
በሀገር ዓቀፍ ደረጃ አንደኛ ዙር በ10 ከተሞች የሥራ ላይ ልምምድ ካደረጉ 15 ሺህ 731 ወጣቶች ውስጥ ለ12 ሺህ 486 ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን በማሳያነት አንስተዋል። በመርሐ ግብሩ ተጠቃሚ ከኾኑ ወጣቶች ውስጥ 60 በመቶ የሚኾኑት ሴቶች ናቸው። መርሐ ግብሩ እንደሚቀጥልም ነው የገለጹት።
ወጣቶች ተወዳዳሪ እንዲኾኑ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
        👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
            
		