
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የጀመራቸውን የአሠራር ማሻሻያዎች፣ የዲጂታላይዜሽን እንዲሁም የዳኝነት እና የፍትሕ አካላትን የትብብር ጥምረት ለማጠናከር እና የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖራቸው ለማስቻል ሁለት አዋጆች እና አንድ ረቂቅ ደንብን አቅርቦ ከምክር ቤት አባላት፣ ከዳኞች፤ ከዐቃቢያነ ሕግ፣ ከሕግ ተመራማሪዎች፣ ከፖሊስ፣ ጠበቆች እና ሌሎች ባለድርሻዎች ጋር የግብዓት ማሰባሰቢያ ምክክር አካሂዷል።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፍርድ ቤቶች አዲስ (ማሻሻያ) አዋጅ፣ የክልሉን ተከላካይ ጠበቆች ጽሕፈት ቤት ለማቋቋም የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ እና የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት አገልግሎት ክፍያን ለመወሰን የተዘጋጀ ረቂቅ ደንብ ቀርቦ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ የሕግ ፣ የፍትሕ እና የዳኝነት አካላት ለረቂቅ የሕግ ማዕቀፎች ግብዓት የሚኾኑ አስተያየቶችን ሰጠውባቸዋል።
ለግብዓት ማሰባሰቢያ ምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሙሉዓለም ቢያዝን ፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አገልግሎት አሰጣጡን ፈጣን፣ ተደራሽ፣ ወጪ ቆጣቢ፣ ነጻ እና ገለልተኛ ለማድረግ የሶስት ዓመት የትራንስፎርሜሽን እቅዱን በመከለስ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውሰዋል። እቅዱን ከግብ ለማድረስ የሚያስችሉ የሕግ ማሻሻያዎችን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እያደረገ እንደሚገኝ የገለጹት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ዛሬ ለውይይት የቀረቡት ረቂቅ ሕጎች የዚህ አካል ናቸው ብለዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ልዩ አማካሪ ረዳት ፕሮፌሰር ወርቁ ያዜ እና በምክትል ፕሬዘዳንት ደረጃ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት አማካሪ ብንያም ዮሃንስ ረቂቅ ሕጎችን ለተሳታፊዎች አቅርበዋል። በቀረቡት ረቂቅ ሕጎች ላይ ከተሳታፊዎች ግብዓት ለማሰባሰብ ውይይቱን የመሩት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው፣ እነዚህ የሕግ ማሻሻያዎች ፍርድ ቤቱ የጀመረዉን የለዉጥ ሥራ የሚያሳልጡ ይሆናሉ ብለዋል። ረቂቅ ሕጎቹ የዳኝት ተቋም ግንባታ ሥራዉ በሕግ፣ በግልጸኝነት እና ተጠያቂነት ባለዉ አሠራር እንዲደገፍ የማድረግ አቅም እንደሚኖራቸው ተናግረዋል። ተሳታፊዎችም በባለቤትነት ስሜት ለረቂቅ ሕጎች መዳበር ግብዓት የሚኾኑ አስተያይቶችን በመስጠታቸው አመስግነው ፣ የተሰጡ አስተያየቶችን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እንደ አግባብነታቸዉ ረቂቅ የሕግ ማዕቀፎችን ለማዳበር እንደሚጠቀምባቸው ተናግረዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በቀረቡ ረቂቅ ሕጎች ላይ ከሰጡት ግብዓት ባሻገር ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አጠቀላይ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡን በመሠረታዊነት ለመለወጥ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አድንቀዉ ፣ ይህንን ለመደገፍ ዝግጁ መኾናቸዉን አረጋግጠዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
