ከ117 ሺህ በላይ አባወራዎችን የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወሸ።

19

ከሚሴ: ታኅሣሥ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና መምሪያ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥራ ያለበትን ሁኔታ ከባለድርሻ አካላት ጋር ገምግሟል። የደዋጨፋ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ያሲን ይማም በወረዳው የጤና መድኅን ተጠቃሚዎች ሽፋንን ለማሻሻል በተሥራው ሥራ በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

የጅሌጥሙጋ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አሕመድ ዑመር ለጤና መድኅን ተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ የመድኃኒት አቅርቦት ለማድረስ በወረዳው የማኅበረሰብ አቀፍ መድኃኒት ቤት በመክፈት በቅናሽ ዋጋ አገልግሎቱን እንዲያገኙ እየተደረገ መኾኑን አስረድተዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ ዑስማን ዓሊ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ117 ሺህ በላይ አባወራዎችን የጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

ከ33 ሺህ በላይ የሚኾኑ አቅመ ደካሞች እና የጤና መድኅን አገልግሎት ክፍያ መክፈል የማይችሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎቱን በነጻ እንዲያገኙ መደረጉንም ኀላፊው ተናግረዋል።

በቀጣይ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የጤና መድኅን ተጠቃሚዎችን ቁጥር ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሠራም አስረድተዋል።

ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሂም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከሁለት አመታት በፊት ወደ ጎዴ መጥቼ ነበር።ከዚያ ወዲህ እየተካሄደ ያለው ለውጥ አበረታች ነው።
Next articleየአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሶስት የተለያዩ ረቂቅ ሕጎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የግብዓት ማሰባሰቢያ ምክክር አካሄደ።