“ፓርቲው ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የገባውን ቃል ከስኬት ለማድረስ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል” ከንቲባ አዳነች አቤቤ

64

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ “ከቃል እስከ ባሕል” በሚል መሪ መልዕክት 2ኛው የብልፅግና ፓርቲ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤ ቅድመ ጉባኤ ውይይት የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ፣ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ እና የኢንስፔክሽንና ሥነ ምግባር ኮምሽን ባቀረበው ረቂቅ ሪፖርት ላይ ውይይት ማካሄድ ጀምረዋል።

በውይይቱ መክፈቻ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በብልጽግና ፓርቲ መሪነት ባለፉት የለውጥ ዓመታት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እሳቤዎች እና ልምምዶችን በተለወጠ እና አዲስ የሆነ የሥራ ባሕል በመተግበር የነዋሪውን ሕይወት መለወጥ ያስቻሉ ስኬቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡

ፓርቲው ከምስረታው ጀምሮ በሁለንተናዊ መስኮች ለውጦችን ለማምጣት የሕዝቦችን ተሳታፊነት እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲሁም ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የገባውን ቃል ከስኬት ለማድረስ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል፡፡

ከነባር እሳቤዎች በመውጣት ተጨባጭ ለውጥ ያመጡ አሰባሳቢ እና አሳታፊ የፖለቲካ እሳቤን በመተግበር፣ የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚን ስርዓትን ወደ ስራ በማስገባት፣ በሰው ተኮር ተግባራት እና በአጠቃላይ ማህበራዊ ዘርፎች የህዝቦችን ተጠቃሚነት ቅድሚያ በመስጠትና በማረጋገጥ፣ ፕሮጀክቶችን አቅዶ በፍጥነት በመተግበር እና ወደ ስራ በማስገባት፣ ስኬታማ ዲፕሎማሲን በማካሄድ እና በመሰል መስኮች ቃል በተግባር የተለወጠበት እና አዲስ የፖለቲካ እና የማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ባህል ለውጥ መምጣቱን የተናገሩት ከንቲባ አዳነች ብልጽግና ፓርቲ በአንደኛው ጉባኤው የገባቸውን ቃሎች በተጨባጭ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

ለቀጣይ ሶስት ቀናት በሚካሄደው የቅድመ ጉባኤ ውይይት የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠል ብሎም የታዩ ክፍተቶችን በቀጣይ ለማረም በሚያስችል ደረጃ በጥልቀት የሚወያዩ ይሆናል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ገጹ እንዳስታወቀው የቅድመ ጉባኤ ውይይቶችና የአባላት ኮንፍረስ እስከ ጉባኤው መዳረሻ ድረስ በድምቀትና በከፍተኛ መነሳሳት ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለክልሎች የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
Next article“ከሁለት አመታት በፊት ወደ ጎዴ መጥቼ ነበር።ከዚያ ወዲህ እየተካሄደ ያለው ለውጥ አበረታች ነው።