እንግዶች ቆይታቸው የተመቸ እንዲኾን ተሠርቷል።

16

ወልድያ: ታኅሣሥ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ለልደት በዓል አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ቀድሞ መጠናቀቁን የሰሜን ወሎ ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ አስታውቋል። የሰሜን ወሎ ዞን ድንቅ የኾኑ የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናትን፣ አሸንድየ እና ሶለልን የመሰሉ ድንቅ ባሕላትን እና ሌሎች አያሌ የቱሪዝም ሃብቶችን የያዘ አካባቢ ነው።

ዞኑ በቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናት እና በሌሎች ታሪካዊ፣ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ የቱሪዝም መዳረሻዎች ጎብኝዎችን የሚያስተናግድ፣ የጎብኝዎች መዳረሻ ነው። ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ከመደራረባቸው አስቀድሞ በአካባቢው የነበረው የቱሪዝም ፍሰት ከፍተኛ ነበር። ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ግን ከፍተኛ የቱሪዝም መዳረሻ የነበረውን አካባቢ ጎድቶት ቆይቷል።

በቅዱስ ላሊበላ የሚከበረው ታላቁ የልደት በዓል የአካባቢውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት እንደሚመልሰው ይጠበቃል። የሰሜን ወሎ ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ገነት ሙሉጌታ በዞኑ አሽንድዬ፣ ሶለል፣ ልደት እና ጥምቀት በድምቀት እንደሚከበሩ ገልጸዋል። የአካባቢው ቱሪዝም ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጀምሮ ጉዳት ደርሶበት መቆየቱንም ተናግረዋል። የሰሜኑ ጦርነት እና አሁን በክልሉ ያለው ግጭትም ቱሪዝሙን እንደጎዳው ነው የተናገሩት።

የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ የሚያነቃቃውን የልደት በዓል በድምቀት ለማክበር መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል። ሰላም ወዳዱ ሕዝብ ልደትን በታላቅ ሥርዓት ለማክበር መዘጋጀቱንም ተናግረዋል። የአገልግሎት አሰጣጡን ማሻሻል እና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን መሥራታቸውን ገልጸዋል።

ሆቴሎች እንግዶችን ለመቀበል መዘጋጀታቸውንም አመላክተዋል። የላሊበላ ሕዝብ የእንግዶችን እግር አጥቦ እና አክብሮ የሚቀበል መኾኑን ነው የተናገሩት። እንግዶች ቆይታቸው የተመቸ እንዲኾን ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል። እንግዶች በስፋት እንዲመጡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምቹ ኹኔታን እየፈጠረ መኾኑንም ተናግረዋል። እንግዶችም በዓሉን ለማክበር ወደ ላሊበላ እየገቡ መኾናቸውን ነው የገለጹት።

የልደት በዓል በችግር ውስጥ የቆዬውን አካባቢ እንደሚያነቃቃም ተናግረዋል። የላሊበላ ሕዝብ ምርት ቱሪዝም ነው ያሉት ኀላፊዋ በልደት እና በጥምቀት በዓል ገቢ የሚሠበሠብ መኾኑን ገልጸዋል። ቱሪዝም ለላሊበላ ትልቁ እና ዋናው የኢኮኖሚ ምንጭ ነው ብለዋል። ከበዓሉ በኋላም የቱሪዝም እንቅስቃሴው እንደሚቀጥል ተስፋ ይደረጋል ነው ያሉት። የቱሪዝም እንቅስቃሴው ወደነበረበት እንደሚመለስ ያላቸውን ዕምነትም ገልጸዋል።

የቱሪዝም እንቅስቃሴው ከበዓል ማግሥትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የአግልግሎት አሰጣጡን የተሻለ ማድረግ እና በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል። ቱሪዝም ስኬታማ እንዲኾን ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባ ነው የተናገሩት። ማኅበረሰቡ ከመንግሥት ጋር በጋራ በመሥራት ሰላሙን መጠበቅ እንዳለበትም አሳስበዋል። ጎብኝዎች ወደ ታላቁ ሥፋራ እንዲመጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የልደት በዓል ለላሊበላ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ፋይዳው ከፍ ያለ ነው” የቅዱስ ላሊበላ እና አካባቢው ቱሪስት አስጎብኝ ማኅበር
Next articleየወባ ሥርጭት አሳሳቢነት