
ወልድያ: ታኅሣሥ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፉ እና ሀገር አቀፍ አስጎብኝዎች የቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናትን እና የአካባቢውን ቅርሶች ለመጎብኘት በስፋት ይመጣሉ። አምሳያ የሌላቸው የላሊበላ አብያተክርስቲያናት የጎብኝዎችን ቀልብ በመሳብ የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲያድግ ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው። በተለይም የልደት በዓል ሲደርስ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ወደ ላሊበላ በብዛት ይመጣሉ።
አስጎብኝዎች እና ሌሎች ደግሞ ከቱሪዝም ተጠቃሚዎች ይኾናሉ። የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓልን ለማክበር እንግዶች እየገቡ ነው። በዚህ በዓል ደግሞ በርካታ እንግዶች የሚገኙበት በመኾኑ የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ከፍ ያደርገዋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል። የቅዱስ ላሊበላ እና አካባቢው ቱሪስት አስጎብኝ ማኅበር ሊቀመንበር እስታሉ ቀለሙ የቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናት ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ እና ባሕላዊ ትሩፋት ያላቸው በመኾናቸው በርካታ እንግዶች እየመጡ ይጎበኟቸዋል ብለዋል።
የልደት በዓል ደግሞ ለላሊበላ እና አካባቢው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ ነው ብለዋል። ለዓመታት በርካታ እንግዶች በረከትን ለማግኘት የልደትን በዓል በላሊበላ ሲያከብሩ መኖራቸውንም አስታውሰዋል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተፈጠሩ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት የጎብኝዎች ቁጥር ቀንሶ እንደነበርም አንስተዋል። ፈውስ እና በረከትን ለማግኘት የሚሹ እንግዶች ረጅም ርቀትን ተጉዘው ወደ ላሊበላ መግባታቸውንም ገልጸዋል።
በዓሉ የበለጠ በቀረበ ቁጥር እንግዶች በስፋት እንደሚመጡ ይጠበቃል ነው ያሉት። 165 የሚደርሱ የላሊበላ እና አካባቢው አስጎብኝዎች የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናትን እና የአካባቢውን ድንቅ ታሪክ ለማስጎብኝት ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸዋል። በሙያቸው ሀገራቸውን፣ ባሕላቸውን እና ታሪካቸውን በተገቢው መንገድ ለእንግዶች እንደሚያስተዋውቁም ተናግረዋል።
ቅርሱን ለማስተዋወቅ በቂ ዝግጅት መደረጉንም አመላክተዋል። የላሊበላ እና አካባቢው የቱሪዝም እንቅስቃሴ በልደት በዓል ብቻ ሳይኾን በሌሎች ጊዜያትም በጥሩ ሁኔታ እንዲቀጥል የአካባቢውን ሰላም አስተማማኝ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። ቱሪዝም ፍጹም ሰላም እንደሚፈልግም ገልጸዋል። ሰላም ከተረጋገጠ በኋላ እንግዶች ወደ አካባቢው እንዲመጡ ለማድረግ መቀስቀስ እንደሚገባም አመላክተዋል።
የቅዱስ ላሊበላ እና አካባቢው አስጎብኝዎች ታሪኩን እና ሃይማኖታዊ ሥፍራዎችን ለማስተዋወቅ ብቁ አቅም እንደላቸው ነው የተናገሩት። ባለፉት ዓመታት ሀገራቸውን በተገቢው መንገድ ሲያስተዋውቁ መቆየታቸውንም ተናግረዋል። ጎብኝዎች ድንቅ የኾኑ የቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናትን እና በአካባቢው ያሉ ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ሥፍራዎችን እንዲጎበኙም ጥሪ አቅርበዋል። ታይቶ የማይጠገበውን ቦታ፣ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን እንዲያዩ እና በረከት እንዲያገኙም ጥሪ እናቀርባለን ነው ያሉት።
የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል እና በሚገባ ለማስተናገድ ዝግጁ መኾናቸውንም ተናግረዋል። የቱሪዝም እንዱስትሪው ከፍ እንዲል በትብብር መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!