
ላሊበላ: ታኅሣሥ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የልደት በዓል በላሊበላ በድምቀት ይከበራል። ልደትን በላሊበላ ለማክበር አስቀድመው የተነሱ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ላሊበላ እየገቡ ነው። በላሊበላ ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ ሆቴሎችም ተዘጋጅተው እንግዶቻቸውን እየተቀበሉ ነው። ገና የሚመጡትንም በጉጉት እየጠበቁ ናቸው።
የቅዱስ ላሊበላ ሆቴሎች ማኅበር ፕሬዝዳንት እና የምዘና ሪዞርት ባለቤት ዮሐንስ አሰፋ በማኅበሩ ውስጥ ከ52 በላይ ሆቴሎች እንደሚገኙ ተናግረዋል። ሆቴሎቹ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽ ጀምሮ ተቸግረው መቆየታቸውን አስታውሰዋል። በችግር ውስጥ የቆዩት ሆቴሎች ለልደት በዓል ተዘጋጅተው እንግዶችን እየጠበቁ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። በዓሉ እየቀረበ ሲመጣ በርካታ ጎብኝዎች እንደሚመጡ ይጠበቃል ነው ያሉት። የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንግዶች በብዛት እንዲገቡ አስቀድሞ በርካታ በረራዎችን እንዲፈቅድም ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስቀድሞ በርካታ በረራዎችን ከፈቀደ እንግዶች በስፋት ይመጣሉ። የላሊበላ የቱሪዝም እንቅስቃሴም ይነቃቃል ብለዋል።
ሆቴሎች በራቸውን ከፍተው እንግዶችን በብዛት እየጠበቁ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የውጭ ሀገር ጎብኝዎች በዓሉ ሲቀርብ በብዛት እንደሚመጡ ይጠበቃሉ ነው ያሉት። እንግዶቻችን ኑ ተዘጋጅተን እየጠበቅናችሁ ነው ብለዋል። ላሊበላ እና አካባቢው ብቸኛ የገቢ ምንጩ ቱሪዝም ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ ቱሪዝም ከሌለ ላሊበላ የለችም፣ ቱሪዝም እንዲነቃቃ እንፈልጋለን፣ የልደት በዓልም የቱሪዝም እንቅስቃሴውን እንደሚያነቃቃው ተስፋ አለን ነው ያሉት። ጎብኝዎች ሲመጡ የላሊበላ ሆቴሎች ብቻ ሳይኾኑ የላሊበላ ከተማ ነዋሪዎችም ተጠቃሚ እንደሚኾኑ ነው የተናገሩት።
ለቱሪዝም እንቅስቃሴ ሰላም ወሳኝ መኾኑንም ገልጸዋል። ሰላም ካለ ላሊበላ በቱሪዝም ተጠቃሚ እንደሚኾን ጥርጥር የለውም ነው ያሉት። ሆቴሎቻችን አዘጋጀተን፣ መንገድ ጠርገን፣ ትልቅ ተስፋ ይዘን እንግዶቻችን እየጠበቅን ነው ብለዋል። የከተማ ነዋሪዎች የተሻለ እንግዶችን እግር እያጠቡ፣ ካላቸው ላይ ለእነርሱ እየሰጡ መኾናቸውን ገልጸዋል።
እንግዶች ቢመጡ ላሊበላን በሰላም ጎብኝተው እንደሚመለሱ ማረጋገጥ እንችላለን። ከመምጣታቸውም አስቀድሞ ማረጋገጥ ይችላሉ ነው ያሉት። ልደትን አብረውን እንዲያከብሩም ጥሪ እናቀርብላቸዋለን ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!