እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም ዘርፍን ለማሳደግ በትኩረት እየሠራን ነው።

14

እንጅባራ: ታኅሣሥ 24/2017 ዓ.ም(አሚኮ) እንጅባራ ዩኒቨርስቲ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሚገኙ የቱሪዝም ዘርፎችን ለማሳደግ በትኩረት እየሠራ መኾኑን አስታውቋል። በዩኒቨርሲቲው የምርምር እና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ክንዴ በአካባቢው ያለውን የቱሪዝም ዓቅም ለማሳደግ ቱሪዝም እና ሆቴል ማኔጅመንት የትምሕርት ክፍል በመክፈት ተማሪዎችን ከማስተማር ባለፈ ልዩ ልዩ ሥልጠናዎችን እየሰጠ እንደኾነ ገልጸዋል።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በርካታ የቱሪዝም ሃብቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ዶክተር ክንዴ የተፈጥሮ ሐይቆች፣ ፏፏቴዎች፣ ጥብቅ ደኖች፣ ሃይማኖታዊ ቦታዎች እና ሌሎችንም የቱሪዝም ጸጋዎችን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ገልጸዋል። በተቻለ ዓቅም “የቱሪዝም ዘርፍን ለማሳደግ በትኩረት እየሠራን ነው” ብለዋል። እስከ አሁን ጸጋዎቹን በመለየት፣ መረጃዎችን አደራጅቶ በመያዝ እና አካባቢዎቹን በማስተዋወቅ በኩል ችግሮች እንደነበሩ ጠቅሰዋል።

በአግልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶችን ዓቅም ለማሳደግ የተሻላ አግልግሎት መስጠት እንዲችሉ የሥልጠና መስጫ ማዕከል በመክፈት ሥራ ማስጀመራቸውን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል። ከተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ሃብቶች በተጨማሪ የአገው ፈረሰኞች ማኅበርን ቱሪስቶች እንዲጎበኙ ለማድረግ ሥራዎች እየተተገበሩ መኾኑን የጠቆሙት ዶክተር ክንዴ ሌሎችንም የቱሪዝም መዳረሻዎች ለማስተዋወቅ የተለያዩ ጥናቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል።

የጸጥታ ችግሩ ጥናት የሚያስፈልጋቸው መዳረሻዎችን ለመፈተሽ እንቅፋት ኾኗል ነው ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ። ችግሩ እስከሚፈታ አሚኮን ጨምር የዩኒቨርሲቲው ማኅበራዊ ትስስር ገጽን በመጠቀም ሃብቶችን የማስተዋወቅ ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ያሉ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ከክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር የቱሪዝም ዘርፎችን ለማስተዋወቅ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውንም አንስተዋል።

ዘጋቢ፡ ሰለሞን ስንታየሁ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በአማራ ክልል ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎች አበረታች ናቸው” ሚኒስትር ድኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ
Next article“ኑ ተዘጋጅተን እየጠበቅናችሁ ነው” የላሊበላ ሆቴሎች ማኅበር