
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት ጉብኝት ወቅት ባደረጉት ንግግር ከታሪክ መማር፣ ታሪክን መዘከር፣ ታሪክን መሥራት ከዚህ ትውልድ ይጠበቃል ብለዋል። እንደ ኢቢሲ መረጃ የነገን ተስፋ ብሩህ ለማድረግ ትናንትን ከዛሬ ጋር ማገናኘት፣ ዛሬን ደግሞ ከነገ ጋር ማስተሳሰር ይጠበቃልም ነው ያሉት።
ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሀገራችንን ክብር እና ዘመናዊነት በጠበቀ መልኩ ወሳኝ ሀገራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች የሚመከሩበት ቦታ አድርገው ማጽናታቸውን አስታውሰዋል። ይህን የታሪክ አሻራ ደረጃውን ከፍ በሚያደርግ መንገድ በማደስ እና በማስዋብ ኢትዮጵያን የሚመጥን እንዲኾን ማድረግ እጅግ የሚያኮራ ተግባር ስለመኾኑም ጠቅሰዋል።
ሀሳቡን በማመንጨት እና ሥራው እንዲሳለጥ በማድረግ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሊመሰገኑ ይገባልም ነው ያሉት። በሀገሪቱ በኮሪደር ልማት ከተማን በማደስ እና ገጠርንም የልማት ማዕከል በማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ብሩህ ተስፋን የፈነጠቁ ስለመኾናቸውም አውስተዋል።
የስንዴ እና የሩዝ እርሻ፣ የሌማት ትሩፋት፣ የአምራች ኢንዱስትሪ፣ የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት እና ሌሎችንም ዘርፎች በአብነት ጠቅሰዋል።
የተጀመረው ሀገራዊ ምክክርም አሳታፊ በኾነ መንገድ እየተካሄደ ስለመኾኑ አፈ ጉባኤው አንስተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!