“ላሊበላ ልዩ ቅርስ ነው፤ ኢትዮጵያም ልዩ ሀገር ናት” ከታይዋን የመጡ ጎብኝ

61

ወልድያ: ታኅሣሥ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በድንቅ ጥበብ የታነጹት የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት የጎብኝዎችን ትኩረት ይስባሉ። ዓለም አቀፍ ጎብኝዎች ከኢትዮጵያ ውጭ የማይታዩትን ድንቅ አብያተክርስቲያናት ለማየት ከሩቅ ተጉዘው ይመጣሉ። የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናትን እየጎበኙ ያገኘናቸው ከታይዋን የመጡ ጎብኝዎች ባዩት ነገር መደነቃቸውን ነግረውናል። የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት ልዩ እና ድንቅ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት ሊ ሁ የህ “ወደ ላሊበላ ስመጣ ለመጀመሪያ ነው፤ ውብ ምድር እና ውብ ሀገር አይቻለሁ” ብለዋል። የላሊበላ የኪነ ሕንጻ ጥበቡ የሚደንቅ መኾኑን ነው የገለጹት። ሕዝቡም ደግ መኾኑን ተናግረዋል። በቆይታቸው እንጀራ እና ሌሎች የኢትዮጵያ ምግቦች እንደተመቻቸውም ገልጸዋል። በላሊበላ ባዩት ነገር ሁሉ እየተደሰቱበት መኾኑንም ተናግረዋል።

ከአሥር ጊዜ በላይ የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናትን የጎበኙት ሮቦርት ሁዋንግ በተደጋጋሚ ባዩት ቁጥር እንደሚደነቁበት ነው የገለጹት። የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት ብቻ ሳይኾኑ በሥፍራው ያሉ አማኞች ኅብረ ዝማሬም የሚገርም መኾኑን ተናግረዋል። መንፈሳዊ ሥርዓቱ እና የአብያተ ክርስቲያናቱ አሠራር የሚደንቅ መኾኑን ገልጸዋል። በመላው ዓለም የሚገኙ ጎብኝዎች ላሊበላን እንዲጎበኙ እና የልደት በዓልን በላሊበላ እንዲያከብሩ ጥሪ አቀርብላቸዋለሁ ነው ያሉት።

የልደት በዓል አከባበር በኢትዮጵያ ከሌሎች ዓለማት ሁሉ የተለየ እና ድንቅ ነው ያሉት ሁዋንግ የኢትዮጵያ የልደት በዓል አከባበር ከምዕራባውያን እና ከሌሎች ዓለማት ሁሉ የተለየ እና የሚደንቅ ነው ብለዋል። ሌላኛዋ ጎብኚ ሊ ሺ ቺያ ሊን “ድንቅ የኾኑ አብያተክርስቲያናት እና ጥልቅ የኾነ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ተመልክቻለሁ” ነው ያሉት።

ከመምጣቴ አስቀድሞ ስለ ኢትዮጵያ ስሰማው የነበረው እና መጥቼ ያየሁት ፈጽሞ አይገናኝም ብለዋል። እርሳቸው ከመምጣታቸው አስቀድሞ በአዕምሯቸው የነበረችው ኢትዮጵያ ደሀ እና ሕዝቦቿም በችግር ውስጥ የሚኖሩ እንደኾኑ ያስቡ እንደነበር ነው የተናገሩት። ከመጡ በኋላ ያዩት ነገር ግን የሚደነቅ መኾኑን ነው የገለጹት።

መጥቼ ካየሁት በኋላ ግን ጥንታዊ ባሕል፣ ሃይማኖት እና ቅርስ ያላቸው መኾናቸውን አይቻለሁ ብለዋል። የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢን ጎብኝተው እንደመጡም ተናግረዋል፡፡ ጎብኝዋ በደቡብ አካባቢ የሚደንቅ ባሕላዊ ሥርዓት አለ፣ ወደ ሰሜኑ ክፍል ደግሞ ቅርስ እና ታሪካዊ ሥፍራዎች እንደሚበዙ ተመልክቻለሁ ነው ያሉት።

ስለ ኢየሱስ እና ስለ ቤተክርስቲያን መምህሬ በስፋት ነግሮኛል፣ በላሊበላ ያሉ አብያተክርስቲያናት እና ሃይማኖታዊ ሥርዓት ግን በየትኛውም ዓለም የሌሉ ናቸው ብለዋል። ባየሁት ነገር እጅግ ተደንቄያለሁ ነው ያሉት። ዓለም አቀፍ ጎብኝዎች ወደ ኢትዮጵያ ቢመጡ ብዙ ነገር ያተርፋሉ፣ እኛ እንዳየነው አይነት የሚያስገርም ሥራ ማየት ይችላሉ ብለዋል። ሕዝቡም የሚገርም ነው። ጎብኝዎች ወደ ኢትዮጵያ ኑ ነው ያሉት።

እንደ ላሊበላ አይነት ቅርስ በየትኛውም ዓለም የለም፣ ይሄ ልዩ ቅርስ ነው፣ ኢትዮጵያም ልዩ ሀገር ናት ነው ያሉት። በላሊበላ የሚደንቅ መንፈሳዊ ሥርዓት ነው ያለው፣ በኢትዮጵያ ያለው ባሕል እና ሃይማኖት እጅግ የሚደነቅ ነው ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየገበያ ማዕከላትን በማስፋት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት በትኩረት እየተሠራ ነው።
Next article“ትናንትን ከዛሬ ጋር ማገናኘት፣ ዛሬን ደግሞ ከነገ ጋር ማስተሳሰር ይጠበቃል” አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ